
ባሕር ዳር: ሐምሌ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ታሳቢ በማድረግ ሀገራዊ ዕድገትን በሚያስቀጥል አግባብ በጥብቅ ቁጥጥር የሚተገበር መኾኑን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ገልጸዋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ በመጀመሪያ እና በሁለተኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሂደት ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ ለመግባት ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ ተመን፣ የገንዘብ እና ፋይናንስ ፖሊሲ፣ የመንግሥት ገቢ እና ወጪ ፊስካል ፖሊሲን በማሻሻል እና ዕዳን በማቃለል የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉ በገበያው እንዲመራ የሚያደርግ ነው ብለዋል። የባንክ፣ ጅምላ እና ችርቻሮ የንግድ ሰንሰለቶችን ለውጭ ተወዳዳሪ በመክፈት በተቀናጀ እና በተናበበ ማዕቀፍ ዕድገትን የሚያስቀጠል የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲኖር የሚያስችል መኾኑን ገልጸዋል።
ሀገራዊ ባለሃብቱን በመደገፍ የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ እና የልማት ድርጅቶችን ውጤታማነት በማሻሻል ጤናማ የንግድ ባንክ ተወዳዳሪነት እና የፋይናንስ ሥርዓት መፍጠር በትኩረት እንደሚሠራባቸው አንስተዋል። የተቀናጀ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተናበበ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክን ጨምሮ በዓለም አቀፍ አጋሮች ድጋፍ የሚተገበር መኾኑን አብራርተዋል።
የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያው እንዲመራ ለማስቻልም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና በብሔራዊ ባንክ ፍኖተ ካርታ ባለፉት ሦስት ዓመታት ዕቅድ ተይዞ ሢሠራበት እንደነበር አስረድተዋል። የንግድ ባንክን ከ850 እስከ 900 ቢሊዮን ብር ዕዳ ገንዘብ ሚኒስቴር በመውሰድ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከዕዳ ነፃ እንዲኾኑ በማድረግ ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት ለመፍጠር ወሳኝነት እንዳለው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማስቀጠል በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና አበዳሪ ሀገራት ድጋፍ ተግባራዊ መደረጉ ዕዳን በመቀስ የውጭ ምንዛሬ ክምችትን ለማሳደግ አመች መኾኑን ተናግረዋል። የፖሊሲ ትግበራውን በከፍተኛ ቅድመ ዝግጅት እና ጥንቃቄ በመምራት የዋጋ ንረት እና የምንዛሬ ገበያ መዋዥቅን እንዲሁም የአጭር ጊዜ ጫናን በመቋቋም የተረጋጋ ኢኮኖሚ መፍጠር ዋነኛ ዓላማ መኾኑን ተናግረዋል።
በዚህም የፖሊሲ ትግበራ እና ድርድሩ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት በማስቀደም የተፈጸመ እና የተገኘው የ4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ቁጠባ ድጋፍ የዕዳ ጫናን ለማቃለል ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መኾኑን ገልጸዋል። የገንዘብ ድጋፉ የሀገርን የዕዳ ጫና በማቃለል ለዝቅተኛ ተከፋይ ሠራተኞች፣ ለከተማ እና ገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች፣ ለማዳበሪያ፣ ለነዳጅ፣ ለዘይት ድጎማ እና ለመደበኛ የልማት ሥራ የሚውል መኾኑን አንስተዋል።
የገንዘብ ድጋፉም በጥብቅ የቁጥጥር ማዕቀፍ በቂ ዝግጅት ተደርጎበት በግልጸኝነት ለልማት ሥራ እና በሪፎርሙ ምክንያት ጫና ሊደርስባቸው የሚችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጎማ የሚውል መኾኑን ገልጸዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሚመራው የማክሮ ኢኮኖሚ ቡድን ለዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ዜጎች ድጎማ የሚኾን የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን አስረድተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እና በገንዘብ ሚኒስቴር ትብብር ለደመወዝ ድጎማ የሚውል የፋይናንስ ቅድመ ዝግጅት ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል። በዚህም የፌዴራል እና የክልል ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ድጎማ ከ90 እስከ 95 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ገንዘብ በፌዴራል መንግስት ወጪ ተሸፍኖ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።
በከተማም ኾነ በገጠር የሚኖሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በነዳጅ ድጎማ እስከ 100 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ድጎማ ማድረግ የሚያስችል በጀት መያዙንም ገልጸዋል። እንደ ኢዜአ ዘገባ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ አርሶ እና አርብቶ አደሩ፣ ሕግ አስከባሪዎች እንዲሁም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የድርሻውን በመወጣት ለፖሊሲው ትግበራ ውጤታማነት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!