
ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቻትቦት የሰው ልጅ የሚያደርገውን ዓይነት የጽሑፍ ወይም የድምፅ ተግባቦት በማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወን የሚያስችል የኮምፒውተር ፕሮግራም ወይም ሶፍትዌር ነው፡፡ የንግድ ድርጅቶች ከደንበኞቻቸው ጋር እና ከሌላ የንግድ ተቋም ጋር ግንኙነት በማድረግ ተግባራትን ማከናወን እንዲችሉ ይረዳል፡፡
ቻትቦቶች ተቋማት ያለ ጊዜ እና ርቀት ገደብ ከደንበኞቻቸው ጋር ቅርብ ኾነው ለመሥራት የሚያስችሉ ናቸው፡፡ በመኾኑም ጊዜን፣ ጉልበትን እና ገንዘብን በመቆጠብ ጉልህ አስተዋጾኦን ያበረክታሉ፡፡ ቀላል ለሚባሉ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሾችን ከመስጠት ጀምሮ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ታግዘው ውስብስብ ሥራዎችን የሚሠሩ የቻትቦት ዓይነቶች አሉ፡፡ ልክ እንደ ሰው ልጅ በድምጽ አሊያም በጽሑፍ ደንበኞች የሚጠይቋቸውን ጥያቄዎች ማስተናገድ የሚችሉ ሥርዓቶች ናቸው፡፡
ብዙ ጊዜ የሚጠየቁ ጥያቄዎችን ከመልሳቸው ጋር አስተሳስሮ የቻትቦት ሥርዓቱ ውስጥ በማስገባት ደንበኞች ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች ውስጥ ቁልፍ ቃላትን በማየት ተቀራራቢ ምላሽ የሚሰጡ የቻትቦት ዓይነቶች አሉ። ከዚህ በተጨማሪም የተፈጥሮ ቋንቋ ቅንብር እና መረዳት (Natural Language Processing እና Natural Language Understanding) እንዲሁም ማሽንን የማስተማሪያ ሞዴሎችን (Machine Learning) በመጠቀም የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በአግባቡ ተረድተው መመለስ የሚችሉ የቻት ቦት ዓይነቶችም አሉ፡፡
አገልግሎታቸውን እና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ተቋማት በቻትቦት ታግዘው መሥራትን ይመርጣሉ፡፡ ምክንያቱም በበይነ መረብ ሥርዓቱን በማሥተሳሰር የ24/ 7 አገልግሎት መስጠት ይችላሉ፡፡ አሁን ላይ በተለያዩ የአገልግሎት ዓይነቶች እየተተገበሩ የሚገኙ ሲኾን የመስመር ላይ ንግድ፣ የደንበኞች አገልግሎት፣ የደንበኞችን መረጃ እና ግብረ መልስ ለማቀናበር እና መሰል ሥራዎች ላይ ውጤታማ የኾነ እገዛ እያደረገ ይገኛል፡፡
ወጭን፣ ጉልበትን እና ጊዜን በመቆጠብ፣ ምርታማነትን በመጨመር፣ የደንበኞችን ግንኙነት በማጎልበት፣ የደንበኞችን ፍላጎት በመረዳት እና በማርካት እንዲሁም ተደራሽነትን በማስፋት ሰፊ ድጋፍ እያደረገ ቢኾንም የቴክኖሎጂው አዲስነት፣ በሰዎች የአረዳድ እና የአጠቃቀም ልዩነት የሚፈጠሩ ውስንነቶች እና የሳይበር ደኅንነት ጉዳይ በአገልግሎቱ ውስጥ ያሉ ፈተናዎች ናቸው፡፡
ቻትቦትን በመጠቀም የደንበኞችን ጊዜ፣ ጉልበት እና ገንዘብ በመቆጠብ እየሠራ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ከተቋሙ ቻትቦት ጋር በመገኛኘት የቲኬት አገልግሎት ማግኘት ይቻላል፡፡ ከአገልግሎት ሰጭዎች ጋር በአካል መገናኘት ሳይጠበቅብን ባለንበት ቦታ በበይነ መረብ ከቻትቦት ሥርዓቱ ጋር በመጻጻፍ በርካታ አገልግሎት እናገኛለን፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!