
ባሕር ዳር: ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማሥተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት እና የሚዲያ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም እንደገለጹት ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለዓባይ ግድብ የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
የግድቡ መሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ከመጋቢት 2003 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ 19 ቢሊዮን 942 ሚሊዮን 519 ሺህ 421 ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል። በተጠናቀቀው የ2016 ዓመት ብቻ ከ1 ቢሊዮን 712 ሚሊዮን 183 ሺህ 820 ብር በላይ መሰብሰቡንም አስረድተዋል።
የዓባይ ግድብ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ እየተገነባ መኾኑን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያውያን የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል። የዓባይ ግድብ ግንባታ መሠረት ድንጋይ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም መቀመጡ ይታወሳል። የግድቡ የውኃ ሙሌት ላለፉት አራት ዓመታት በስኬት ተከናውኗል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!