
ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ባሳለፍነው ሳምንት 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኮምፒውተሮች እንዳይሠሩ ያደረገ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መቋረጥ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ተከስቶ በርካታ አገልግሎቶችን መስተጓጎላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ በ2011 ተመሥርቶ በ170 ሀገራት የደኅንነት ቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን የሚያቀርበው ክራውድስቲክ የተባለ ድርጅት ለተገልጋዮቹ በላከው ኮራፕት ያደረገ የሶፍትዌር ማሻሻያ ምክንያት መቋረጡ እንደተፈጠረ ተሰምቷል።
በዓለማችን ከተመዘገቡ የሳይበር ጉዳቶች መካከል ብዙ ኮምፒውተሮችን በማስተጓጎል እና ተቋማት አገልግሎታቸውን መስጠት እንዳይችሉ በማድረጉ አስከፊ ኾኖ ተመዝግቧል፡፡ ኮራፕት ያደረገ ሶፍትዌር ማለት በሀርድዌር አሊያም በሶፍትዌር ብልሽት ምክንያት መሥራት የማይችል ሶፍትዌር ማለት ነው፡፡ ማሻሻያው ከተላከ በኋላ 8 ነጥብ 5 ኮምፒውተሮች ችግር አጋጥሟቸዋል፡፡
በሙያዊ አጠራሩ ቡት ሉፕ ወይም ኮምፒውተሮቹ ለመክፈት መቸገር እና ደጋግመው ሪስታርት የማድረግ ችግር ያጋጠማቸው ሲኾን የክራውድስቲክን አገልግሎት የሚጠቀሙ ባንኮች፣ የጤና ተቋማት፣ የአቪየሽን አገልግሎት እና ሌሎችም ግንኙነት ያላቸው የተቋማት ሥርዓቶች መቋረጥ ገጥሟቸዋል፡፡
ቴክኖሶሊውሽን ድረ ገጽ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መቋረጥ በብዙ ምክንያቶች ሊፈጠር የሚችል መኾኑን ያስረዳል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ለአገልግሎት የሚውሉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች በሚያጋጥማቸው ብልሽት፣ ሰዎች በሚፈጥሯቸው ስህተቶች፣ በተፈጥሮ አደጋ፣ ደኅንነታቸው ባልተጠበቁ ሶፍትዌሮች፣ በሳይበር ጥቃቶች እና በኀይል መቆራረጥ ችግሩ ሊከሰት እንደሚችል ይገልጻል፡፡
ሰዎች የሚፈጥሯቸው ስህተቶች ተብለው የተገለጹት በግንባታ ወይም ሌላ ምክንያት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ላይ በሚደርሷቸው አደጋዎች የሚፈጠርን መቆራረጥን ለመግለጽ ነው፡፡ ለምሳሌ የተቀበሩ የግንኙነት መስመሮች በቁፋሮ ወቅት ቢቆረጡ አሊያም በአየር ላይ የተዘረጉ ገመዶች ላይ ጉዳት ቢደርስ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መቋረጥ ሊያስከትል ይችላል፡፡
የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተት እና መሠል የተፈጥሮ አደጋዎችም በተዘረጉ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ሥርዓቶች ላይ ጉዳት በማድረስ ችግሩ እንዲከሰት ያደርጋሉ፡፡ በአጠቃላይ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መቋረጥ ኾን ተብሎ የሚፈጸም እና ሳይታሰብ የሚፈጸም ተብሎ በሁለት ይለያል፡፡
አሁን ላይ በክራውድስቲክ የማሻሻያ ሶፍትዌር አማካኝነት የተከሰተው መቋረጥ ሳይታወቅ ሶፍትዌሩ ኮራፕት በማድረጉ ምክንያት የተፈጠረ ነው፡፡ በተቋማት ላይ ጥቃት ለማድረስ ታልሞ በሀከሮችም ይህን መሰል ችግር ሊከሰት ይችለል፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር ከዚህ በፊት በ2017 ዋናክራይ በተባለ የሳይበር ጥቃት በ150 ሀገራት የሚገኙ 300 ሺህ ኮምፒውተሮች ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡
በ2021 ደግሞ ሜታ ኩባንያ ላይ ለ6 ሰዓታት የቆየ መቋረጥ ተከስቶ እንደነበረም ይታወሳል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!