
ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኀብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ አሰጣጥ ማሳለጫ ማዕከል አስተባባሪ አሞኜ በላይ እንዳሉት ኮሌራ በክልሉ በ2015 ዓ.ም በ16 ዞኖች እና በ58 ወረዳዎች በመከሰት 5 ሺህ ያህል ሰዎችን አጥቅቶ 90 ሰዎችን ለህልፈት መዳረጉን አስታውሰዋል።
በወቅቱም መንግሥት፣ አጋር አካላት እና ኀብረተሰቡ ባደረጉት ርብርብም በሽታውን መቆጣጠር መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡
አስተባባሪው አሁን እንደገና በሽታው አገርሽቶ በአጭር ጊዜያት ውስጥ ወረርሽኝ ደረጃ ላይ ደርሷል ነው ያሉት።
እንደ አስተባባሪው ገለጻም ወረርሽኙ በባሕር ዳር ከተማ እና በዙሪያ ወረዳው፣ በሰሜን ጎጃም፣ በጎንደር ከተማ እና በዙሪያ ወረዳው፣ በማዕከላዊ ጎንደር፣ ምዕራብ ጎንደር እና በደቡብ ጎንደር ዞኖች በስፋት ተስፋፍቷል ነው ያሉት። በርካታ ኀብረተሰብም በወረርሽኙ ተጠቅቷል ብለዋል።
“በተለይ ንጹህ የመጠጥ ውኃ እና የመጸዳጂያ ቤቶች በሌሉባቸው የተፈናቃይ የመጠለያ ጣቢያዎች፣ የጸበል ሥፍራዎች፣ በሰፋፊ የእርሻ አካባቢዎች እና ኀብረተሰቡ ተፋፍጎ በሚኖርባቸው አካባቢዎች ወረርሽኙ በፍጥነት በመስፋፋቱ ሰዎችን እያጠቃ ነው” ሲሉ አስተባባሪው ተናግረዋል።
አቶ አሞኜ ወረርሽኙን ኀብረተሰቡ ውኃን አክሞ ወይም አፍልቶ በመጠጣት፣ በመጸዳጂያ ቤት በአግባቡ በመጠቀም፣ ምግብን አብስሎ በመመገብ እና የግል ንጽህናን በመጠበቅ በተለይ ደግሞ እጅን በሳሙና በመታጠብ በቀላሉ መቆጣጠር እንደሚችል ገልጸዋል።
የኮሌራን ክትባት እንዲሁም የሕክምና አገልግሎቱ በአቅራቢያ በሚገኝ የጤና ተቋም ሁሉ ስለሚሰጥ ሕክምናውን በአግባቡ በመውሰድ በሽታውን መግታት እና መቆጣጠር እንደሚቻልም ነው አቶ አሞኜ ያብራሩት።
አንድ በኮሌራ በሽታ የተጠቃ ሰው ካልታከመ በአምስት ቀናት ውስጥ ሕይዎቱን ሊያጣ እንደሚችል የጠቆሙት አስተባባሪው በቀላሉም ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላው አካባቢ በመዛመት በፍጥነት ገዳይ እንደኾነም ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!