
ባሕር ዳር: ሐምሌ 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ክላውድ ኮምፒውቲንግ የሚለው ቃል ብዙ ጊዜ ሲጠራ የምንሰማው ነው። ነገር ግን በውስጡ ብዙ ሙያዊ የኾኑ ጽንስ ሃሳቦች ያሉበት በመኾኑ የምንረዳበት መንገድ ሊለያይ ይችላል።
የመተግበሪያ እና የሀርድዌር ለምሳሌ የመረጃ ማከማቻ የመሳሰሉ የሳይበር መሠረተ ልማቶችን በራስ አቅም ለማሟላት እያደገ የሚሄድ የመረጃ መጠን ለሚኖራቸው ተቋማት ፈታኝ የሚኾንበት ሁኔታ አለ። ለምሳሌ የመረጃ ማከማቻ በየጊዜው እየገዙ ለመጠቀም መሞከር ከመረጃ ደኅንነት፣ ከጊዜ፣ ከገንዘብ፣ ከጉልበት እና ከቀላልነት አንፃር አስቸጋሪ ስለሚኾን የመረጃ ማዕከል ገንብተው ከርቀት በበይነ መረብ በተሳሰረ ስልት አገልግሎቱን ከሚሰጡ ተቋማት መጠቀም ይቻላል።
ከርቀት በመኾን የሶፍትዌር እና የUርድዌር አገልግሎቶችን የምናገኝበትን ቴክኖሎጂ ክላውድ ኮምፒውቲንግ በማለት እንጠራዋለን። ቴክኖሎጂው የተለያዩ የሳይበር ሥራዎችን ከርቀት ኾነን የምንሠራበት ቴክኖሎጂ ነው። ለምሳሌ ጂሚል፣ ማኅበራዊ ትሥሥር መንገዶች፣ የድረ ገጽ የመረጃ ቋት እና መሰል የዕለት ከዕለት የምንገለገልባቸው የመረጃ አማራጮቻችን በበይነ መረብ በመታገዝ ከርቀት ያለን አገልግሎት በኮምፒውተራችን አሊያም ስልኮቻችን ላይ ኾነን እንድንገለገልባቸው ያግዛል።
ክላውድ ኮምፒውቲንግ ከአገልግሎት አንፃር በሦስት ይከፈላል። የአገልግሎት መሠረተ ልማት የሚያቀርብ፣ መደላድሎችን የሚያቀርብ እና የመተግበሪያ አገልግሎት የሚሰጥ ብለን እንጠራቸዋለን። የመረጃ ቋት እና የሰርቨር (ለልዩ ተግባር የተዘጋጀ ኮምፒውተር) አገልግሎትን በበይነ መረብ ከርቀት በማስተሳስር በኪራይ የምናገኝበት መንገድ የመሠረተ ልማት የሚያቀርበ የክላውድ አገልግሎት ይባላል።
በቀላል ለመረዳት ይቻል ዘንድ የተቋማት ድረ ገጾች የመረጃ ማስቀመጫ መሳሪያዎች ዋጋ አዋጭ ኾኖ ካላገኙት ከርቀት ኾነው የመረጃ ማስቀመጫ የሚያከራዩ ድርጅቶች ላይ በመከራየት አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ። ለዚህ አገልግሎት ቅርብ የኾኑ ምሳሌዎቻችን የተለያዩ ፋይሎችን ከርቀት የምናስቀምጥባቸው ድሮፕቦክስ፣ ጉግል ድራይቭ እና ማይክሮሶፍት ስካይ ድራይቭ የመሳሰሉ የክላውድ ፋይል ማስቀመጫዎች ተጠቃሽ ናቸው።
መደላድሎችን የሚያቀርቡ የክላውድ ኮምፒውቲንግ አገልግሎት የሚያቀርቡ ድርጅቶች ደግሞ በበይነ መረብ ላይ የዌብ እና እኘሊኬሽን ዴቨሎፕመንት ሥራዎችን እንድንሠራ ያግዛሉ። ሦስተኛው መተግበሪያዎችን ከርቀት ኾነን የምንጠቀምበት አገልግሎት ሲኾን በኮምፒውተራችን ወይም ስልካችን ላይ መተግበሪያዎችን መጫን ሳይኖርብን በበይነ መረብ በነፃ አሊያም በኪራይ መጠቀም የምንችልበት ነው።
ክላውድ ኮምፒውቲንግ መጠቀም በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት ። ከእነዚህ ውስጥ ገንዘብን እና ጊዜን ይቆጥባል፣ ፈጣን አገልግሎት ይሰጣል እንዲሁም የመረጃ ደኅንነት እንዲጠበቅ ያደርጋል። እንዲህ ዓይነቱ አገልግሎት የተጀመረው በ1970ዎቹ አካባቢ ሲኾን ክላውድ ኮምፒውቲንግ በሚል መጠራት የጀመረው ግን ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ነው።
አሁን ላይ የመረጃ ማዕከል ገንብተው ይህን አገልግሎት እየሰጡ ካሉ ተቋማት ውስጥ ጉግል፣ አማዞን፣ አራክል፣ ማይክሮሶፍት እና ሲስኮን መጥቀስ እንችላለን ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!