
ባሕር ዳር: ሐምሌ 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የኮምቦልቻ ከተማ ተለዋጭ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታውቋል። 7 ነጥብ 58 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የአስፋልት ተለዋጭ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በመልካም አፈጻጸም ላይ ነው።
የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈጻጸም 16 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታውቋል። የተለዋጭ መንገድ ግንባታው ከፌደራል መንግሥት በተመደበ 1 ቢልየን 138 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተሰራ ነው። የጸጥታ ስጋት፣ በመንገድ ወሰን ክልል ውስጥ የውኃ እና መብራት መሠረተ ልማቶች እንዲሁም ንብረቶች በወቅቱ አለመነሳት የፕሮጀክቱ ፈተናዎች መኾናቸው ተመልክቷል።
ችግሩን ለመቅረፍ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የኮምቦልቻ አካባቢ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ ይገኛል ተብሏል። የመንገዱ መገንባት ወደ ደረቅ ወደብ የሚገቡ እና የሚወጡ ከባድ ተሽከርካሪዎች ተለዋጭ መንገዱን ተጠቅመው ወደ መዳረሻቸው በፍጥነት እንዲደርሱ ያስችላል ተብሏል።
ተለዋጭ መንገዱ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ከባድ ተሸከርካሪዎች ወደ ከተማው መግባት ሳይጠበቅባቸው አቋርጠው ማለፍ ያስችላቸዋል። ከተማዋ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች መዳረሻ እንደመኾኗ የመንገዱ መገንባት ለኢንዱስትሪ ግብዓት እና ምርት ማንቀሳቀሻ በመኾን ያገለግላል።
ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት እንዲኾን አሁንም ያልተፈቱ የወሰን ማስከበር ችግሮች በመኖራቸው በአካባቢው የሚገኙ የመሥተዳድር አካላት እና የከተማዋ ነዋሪዎች አስፋላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ጠይቋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!