
አዲስ አበባ: ሐምሌ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮ ቴሌኮም የ2016 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ይፋ አድርጓል። ተቋሙ በበጀት ዓመቱ በርካታ ስኬቶችን ያገኘበት እንደነበርም የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ተናግረዋል። ተቋሙ ከተጣራ ትርፍ አኳያ 20 ነጥብ 9 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም ተናግረዋል።
ሥራ አስፈጻሚዋ በመግለጫው እንዳነሡት በስትራቴጂ፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ በምርት እና አገልግሎት እንዲሁም የገጠሩን ክፍል የዲጅታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ ስኬቶች የታዩበት ዓመት እንደነበር ገልጸዋል። ኢትዮ ቴሌኮም በአጠቃላይ ተጠቃሚ ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር እድገት እንዳሳየም በመግለጫው ተነስቷል።
በ2016 የቴሌኮም ደምበኛ ቁጥር 78 ነጥብ 3 ሚሊዮን እንደደረሰም አሳውቀዋል። ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸርም 8 ነጥብ 9 በመቶ እድገት ማሳየቱንም አስረድተዋል። በበጀት ዓመቱ የቴሌብር ተጠቃሚ ቁጥር ወደ 47 ነጥብ 55 ሚሊየን ማድረስ መቻሉን አንስተዋል። በዓመቱም በቴሌብር 1 ነጥብ 8 ትሪሊዮን ብር መዘዋወሩ በመግለጫው ተመላክቷል።
ኢትዮ ቴሌኮም ማኅበራዊ ኀላፊነትን ከመወጣት አኳያም በዓመቱ 694 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ማድረጉ ታውቋል። ከ300 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው ተመላክቷል። የውጭ ምንዛሬ፣ የኀይል አቅርቦት፣ በቴሌኮም መሠረተ ልማቶች የነበሩ ስርቆቶች፣ የሰላም መደፍረስ፣ የጥሬ እቃ አቅርቦት እና የዋጋ ግሽበት ትልቅ ፈተናዎች እንደነበሩም ፍሬሕይወት ታምሩ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ኃይለኢየሱስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!