
ሁመራ: ሐምሌ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ)”የምትተከል ሀገር፣ የሚያጸና ትውልድ “በሚል መሪ መልእክት በሀገር ደረጃ እየተካሄደ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በወልቃይት ወረዳ ተጀምሯል።
ኅብረተሰባቸውን በሙያቸው ከማገልገል ባሻገር ለአፈርና ውኅ ጥበቃና የኢኮኖሚ ጠቀሜታ የሚሰጡ ችግኞች መትከላቸውን አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ የመንግሥት ሠራተኞች ገልጸዋል። ችግኝ ከመትከል ባሻገር በየወቅቱ በመገኘት ለተከሉት ችግኝ እንክብካቤን በማድረግ እንዲጸድቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።
የወልቃይት ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጠይብ አብዱ በ2015 በጀት ዓመት 63 ሺህ ችግኝ በወረዳው መተከሉን አንስተው ከ49 ሺህ በላይ ችግኞች መጽደቃቸውን ገልጸዋል። በዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር 56 ሺህ የጽድ ፣ የሚም እና የወይራ ችግኞችን በ20 ሄክታር መሬት ለመትከል እየተሠራ ነው ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገብረ እግዚአብሔር ደሴ የወልቃይት ጠገዴ መልክዓ ምድር በአረንጓዴ መቀነት የታጠቀ ቢኾንም የደን ሃብቱን ለማሳደግ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የመንግሥት ሠራተኞች በመሳተፋችሁ ልትመሠገኑ ይገባል ብለዋል።
ዞኑ ያለ በጀት የሚንቀሳቀስ ቢሆንም በአረንጓዴ አሻራ ልማት ይበልጥ ተሳታፊ ለመኾን በቁርጠኝነት እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። በዞኑ በ2016 በጀት ዓመት ከ6መቶ 20 ሺህ በላይ ችግኝ እንደሚተከል አንስተው ለዚህም ከ80 ሺህ በላይ ጉድጓድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል ።
ሕወሓት ሥልጣን ላይ በቆየበት ዘመን በዞኑ የደን ጭፍጨፋ በስፋት መፈጸሙን አስታውሰው በቀጣይ የአካባቢውን የደን ሃብት ለማሳደግ እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!