የ12ኛ ክፍል ፈተና በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ጥሪ አቀረበ፡፡

28

ባሕር ዳር: ሐምሌ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የ12ኛ ክፍል ፈተናን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የ12ኛ ክፍል ፈተና ለማስፈተን ባስተማሩ አካባቢዎች ሁሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውንም ተናግረዋል። ለቅድመ ዝግጅቱ ባለድረሻ አካላት በቅንጅት መሥራታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

የነበረው ቅንጅታዊ አሠራር ተማሪዎች ተፈትነው ወደ ቤታቸው እስኪመለሱ ድረስ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡ ብሔራዊ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ከባለፉት ዓመታት የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ለየት ባለ ትኩረት እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡት ውጤቶች ለየት ያለ ትኩረት እንዲሰጡ እንዳደረጋቸውም አስታውቀዋል፡፡ ማስተማር በተቻለባቸው አካባቢዎች የተለየ ድጋፍ እና ክትትል ሲደረግ መቆየቱንም አንስተዋል፡፡

የትምህርት ይዘቶቹ እንዲሸፈኑ፣ በኮሌጆች፣ በዩኒቨርሲቲዎች ወርክሾፖች እየተዘጋጁ እንዲሰጡ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት ከወትሮው በተለየ መንገድ እንዲሰጥ እና ሞዴል ፈተና እንዲፈተኑ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የአዳር ጥናት ተዘጋጅቶ እንዲያጠኑ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በአዳር ጥናት ተማሪዎች የተሻለ ተነሳሽነት እንዲኖራቸው እንዳደረገም ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩ የውጤት መዘቅዘቅ በተማሪዎች እና በመምህራን ላይ ቁጭት መፍጠሩን የተናገሩት ኀላፊዋ የመምህራን ቁጭት ተማሪዎችን በተለየ መንገድ እንዲያግዙ እንዳደረጋቸውም አንስተዋል፡፡ በአንዳንድ ከተሞች ላይም ልዩ ትምህርት ቤት በማዘጋጀት ተማሪዎች እንዲዘጋጁ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡ ዪኒቨርሲቲዎችም ለተፈታኝ ተማሪዎች ትምህርት ሲሰጡ መቆየታቸውንም ገልጸዋል፡፡

የ12ኛ ክፍል ፈተና በብየነ መረብ እና በወረቀት እንደሚሰጥ ያነሱት ኀላፊዋ ደሴ፣ ጎንደር እና ባሕር ዳር ከተሞች በበይነ መረብ ይሰጣል ነው ያሉት፡፡ ተማሪዎች በተያዘለት ጊዜ ፈተናቸውን እንዲወስዱ ዩኒቨርሲቲዎች እየሠሩ መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ጋር በመኾን ፈተናው ስኬታማ ኾኖ በሚሰጥበት መንገድ መወያየታቸውንም ገልጸዋል። ፈታኞችም ወደሚፈትኑባቸው አካባቢዎች እየገቡ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

የክልሉ የፈተና ግብረ ኀይል ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በጥምረት እየሠራ መኾኑንም አስረድተዋል፡፡ ፈታኞችን፣ ተፈታኞችን እና ፈተናን የማጓጓዝ ሥራ በልዩ ትኩረት እየተሠራበት መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ ከሐምሌ 3/2016 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 5/2016 ዓ.ም የማኅበራዊ ሳይንስ ፈተና እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡ ከሐምሌ 9/2016 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም ደግሞ የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡

በሁለቱም የትምህርት መስኮች በመጀመሪያው ዙር 96 ሺህ 408 ተማሪዎች ፈተናውን ይወስዳሉ ነው የተባለው፡፡ ሁለተኛ ዙር ፈተና እንደሚኖርም ተመላክቷል፡፡ በመጀመሪያው ዙር በ375 የፈተና ጣቢያዎች እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎቹ ከ390 ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡ ተማሪዎች በሰላም ተፈትነው እስኪመለሱ ድረስ የሁሉም ትብብር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

ወላጆች ተማሪዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈተኑ ማበረታታት እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል፡፡ የብሔራዊ ፈተና ያለ ምንም ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ፈተናውን የሚያደናቅፍ ማንኛውንም ነገር መታገል ከማኅበረሰቡ እንደሚጠበቅም አንስተዋል፡፡

የመማር ማስተማሩን ስብራት መጠገን የሚቻለው ሁሉም መረባረብ ሲችል መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ እስካሁን የተሠራው ሥራ በውጤት የሚለካው ፈተናው በሰላም ሲሰጥ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ክልሉ የሚጠበቅበትን ያክል ተማሪ ባያስተምርም የሚፈተኑት ተማሪዎች ጥሩ ውጤት እንዲያመጡ እና ክልሉን ከሌሎች ክልሎች ጋር ተወዳዳሪ እንዲያደርጉ የሁሉም ሰው እገዛ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

በአማራ ክልል መማር ከነበረባቸው 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተማሪዎች መካከል በ2016 የትምህርት ዘመን ማስተማር የተቻለው 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ተማሪዎች ነው ተብሏል፡፡ በክልሉ መማር ከሚገባቸው ተማሪዎች መካከል መማር የቻሉት 58 ነጥብ 62 በመቶ ብቻ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ ያልጀመሩ ዞኖች እና ወረዳዎች መኖራቸውም ተመላክቷል፡፡

በመጀመሪያው ዙር የሚፈተኑ ተማሪዎች በትክክል ተምረው የሚገባውን ትምህርት የሸፈኑ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ሌሎች ተማሪዎች እንደሚፈተኑ ነው የተገለጸው፡፡ በመጀመሪያው ዙር የተፈተኑ ተማሪዎች በሁለተኛው ዙር መፈተን እንደማይችሉም ተናግረዋል፡፡ በበይነ መረብ የሚፈተኑ ተማሪዎችን የማለማመድ ሥራ ሢሠራ መቆየቱን የተናገሩት ኀላፊዋ በበይነ መረብ የሚፈተኑት ብቁ የኾኑ ተማሪዎች ብቻ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ተፈታኝ ተማሪዎች ለፈተና ዝግጁ እንዲኾኑ የሥነ ልቦና ዝግጅት ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአይከል ከተማ አስተዳደር የሰላም ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።
Next articleጤና ተቋማት ለማኅበረሰቡ በተሟላ መንገድ አገለግሎት እንዲሰጡ ሁሉም ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ተባለ።