“የታጠቁ ወገኖች ከግጭት እና ጦርነት ወጥተው ተቀራርበው ችግሩን በመፍታት ሰላማችንን ያስፍኑልን” የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች

24

ባሕር ዳር: ሰኔ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በባሕር ዳር ከተማ የጣና ክፍለ ከተማ ሴቶች ”ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም“ በሚል መሪ መልእክት የሰላም ኮንፈረንስ አካሂደዋል፡፡

በኮንፈረንሱ በሰላም መደፍረስ ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮች ተነስተዋል፡፡

በኮንፈረንሱ የተሳተፉት አስተያየት ሰጪዎች በሰላም እና በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ሰርተው ለማደር መቸገራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ በከተማዋ የተባባሰው ቅሚያ እና ዝርፊያ ሕዝቡን ማሳቀቁን ተናግረዋል፡፡

ስለኾነም ችግሩ በሰላም እና በውይይት እንዲያልቅ ጠይቀዋል፡፡ የታጠቁ ወገኖች ወንድም እና ልጆቻችን ናቸው፤ በመኾኑም “ከግጭት እና ከጦርነት ወጥተው ተቀራርበው ችግሩን በመፍታት ሰላማችን ያስፍኑልን” ብለዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ጌትነት አባት የተነሱት አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ገንቢ መኾናቸውን ጠቅሰው ጫካ የገቡ ወንድሞች አጀንዳቸውን አቅርበው በውይይት መፍታት ይገባቸዋል፤ ለዚህም እናቶች እና እህቶች መክራችሁ እንዲመለሱ ማድረግ አለባችሁ ብለዋል፡፡

የልማት እና መልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ሰላም በሰፈነ ጊዜ የሚፈቱ ናቸው ያሉት አቶ ጌትነት ጥያቄዎችንም ለመመለስ ከተማ አሥተዳደሩ እየሠራ መኾኑን አብራርተዋል፡፡

ግጭቱ በሰላም እንዲፈታ ውይይት እና ምክክር አማራጭ የለሽ መፍትሄ ነው ያሉት አቶ ጌትነት እናቶችም ለዚህ ጠንክረው እንዲሰሩ ይፈለጋል ብለዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ በሰላም ኮንፈረንሱ ከሴቶች የሚጠበቀውን የሰላም ፍላጎት እና ምክር አግኝተናል ብለዋል፡፡ በማኅበራዊ ዘርፍ የተነሱትን ችግሮች ወስደን ለመቅረፍ እንሠራለን ነው ያሉት፡፡

ዛሬ ላይ የሰላም እጦቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ የመኖር አለሞኖር ጉዳይ ስለኾነ ለሰላም መሥራት እና መቆም አለብን ያሉት ኀላፊዋ ጫካ ላይ ያሉ ወንድሞቻችንን ለውይይት እና ለንግግር መመለስ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስመረቀ ።
Next article“በሃሳብ የበላይነት በማመን እና ተባብሮ በመሥራት የሰላም እንቅፋቶችን ማስወገድ ይገባል” የደሴ ከተማ ነዋሪዎች