
ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመረጃ እና ተግባቦት ቴክኖሎጂ እድገት እጅግ ግሩም በኾነ ፍጥነት እየረቀቀ መጥቷል። በይነ መረብ ደግሞ ሰዎች የቦታ ርቀት ሳይገድባቸው የትም ኾነው የትኛውንም ዓይነት መረጃ ያለሥጋት መለዋወጥ እንዲችሉ ረድቷል። ዘመን የወለዳቸው የማኅበራዊ ትስስር መንገዶች የመረጃ ልውውጥን ፈጣን በማድረግ የዕለት ከዕለት ሕይወታችንን አቅልሏል።
በመረጃ ልውውጥ ሂደት ከሚፈጠሩ ችግሮች ውስጥ የሦስተኛ ወገን ያልተፈቀደለት ጣልቃ ገብነት ነው። በላኪ እና ተቀባይ መካከል ምሥጢራዊ ወይም ሦስተኛ ወገን ሊያያቸው የማይገባቸው መረጃዎች በተለያየ መንገድ ሲሾልኩ በግለሰብም ኾነ በተቋም ደረጃ የሚፈጥረው ጉዳት አለ። ይህ ጉዳት ቁሳዊ ወይም ሥነ ልቦናዊ ሊሆን ይችላል። የግለሰቦች ምሥጢራዊ መረጃ ሾልኮ ለሦስተኛ ወገን ሲደርስ ስም፣ ክብር እና ዝናን ሊያጎድፍ ይችላል። እንደ መረጃው ይዘት ሌላም ዓይነት ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። በተቋማት ደግሞ ከባድ የኾነ በገንዘብ የሚገመት አሊያም ቀጥተኛ የገንዘብ ኪሳራ ሊደርስ ይችላል።
መረጃ በመላክ እና በመቀበል ሂደት ያለን የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ለመከላከል ከ 4 ሺህ ዓመት በፊት ግብፃውያን ሃይማኖታዊ ይዘቶችን የሚመሠጥሩበት መንገድ ነበር ። ከግብፃውያን በተጨማሪ በግሪክ እና በሮማም ለወታደራዊ አገልግሎት ይውል ነበር። በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ያሉ ለውጦች የምሥጠራን ዘዴ እና ዓይነት እያዘመኑ አሁን ላይ በዲጂታል ዓለም ያለን የመረጃ ልውውጥም ከሰርጎ ገብ ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል መንገድ ኾኗል።
“ምሥጠራ” ማለት መረጃን ወደ ምሥጢራዊ ቅጽ፣ ከተፈቀደለት ሰው ውጭ መረዳት ወደ ማይቻልበት ይዘት ወይም ትርጉም ወደማይሰጥ የምልክቶች ስብስብ የሚቀየርበት መንገድ ነው። ታማኝ ባልኾነ የመረጃ ሥርዓት ደኅንነቱ በተጠበቀ መንገድ መልዕክት / መረጃ ከላኪ ወደ ተቀባይ የሚላክበት መንገድም ነው።
በመረጃ ልውውጥ ብቻ ሳይኾን በተቀመጡ የግል ወይም የተቋም ምሥጢራዊ መረጃዎች ላይ የሚተገበርም ነው – ምሥጠራ ። በዲጂታል መገልገያዎቻችን የምናስቀምጠው ይዘት ከተፈቀደለት ሰው ውጭ ትርጉም የሚሰጥ እንዳይሆን የምናደርግበት ዘዴም ነው። ምሥጠራ ራሱን የቻለ ሰፊ ሳይንስ ሲኾን ይህን የሚያጠናው ሳይንስ ደግሞ “ክሪፕቶግራፊ” ይባላል።
በዘመናዊ ሳይንስ ሦስት ነገሮች በሂደቱ ውስጥ ይገኛሉ። የመጀመሪያው እንዲመሠጠር የተፈለገ መረጃ በሳይንሳዊ አጠራሩ ፕሌን ቴክስት፣ መመሥጠሪያ ሥልተ ቀመር /አልጎሪዝም ፣ ትርጉም ወደማይስጥ ቅርጽ የቀየርነው ጽሑፍ / ሳይፈር ቴክስት እና የመክፈቻ ቁልፍ / ዲክሪፕሽን ኪይ ናቸዉ። ይዘቶች ለመመሥጠሪያ በመረጥነው ሥልተ ቀመር ለመረዳት ወደማይቻል ቅጽ ይቀየሩ እና እንዲደረሰው ወይም እንዲያየው ወደምንፈልገው አካል እንልካለን። የተላከለት አካል ደግሞ ላኪው በሚሰጠው የመክፈቻ ቁልፉ / ዲክሪፕሽን ኪይ ከፍቶ መመልከት ይችላል።
ምሥጠራ በእረፍታ / Data at-rest / ላይ ላሉ እና በእንቅስቃሴ ላይ ያለን መረጃ ደኅንነት ለመጠበቅ ይጠቅማል። በእረፍታ ላይ ያለ መረጃ ማለት በመረጃ ቋት አሊያም በኮምፒውተራችን ተቀምጠው የሚገኙትን ለመግለጽ ሲኾን በእንቅስቃሴ ላይ ያለ መረጃ ማለት ደግሞ ከኮምፒውተር ወደ ኮምፒውተር በመረጃ መረብ አማካኝነት የሚኖር የመረጃ እንቅስቃሴ ወይም ልውውጥ ነው።
ምሥጠራ በብዙ ሁኔታዎች ይከናወናል፡፡ በገንዘብ ልውውጥ፣ በመሥመር ላይ ንግድ /online Business/ ወይም ምሥጢራዊ መረጃዎችን በመላላክ ሂደት ይተገበራል። የንግድ እንቅስቃሴዎች ደኅንነት አሁን ላይ በብዙ መልኩ በምሥጠራ ላይ የተመሰረቱ ናቸው ። ምሥጢራዊ መረጃዎችን በበይነ መረብ ወይም በአካባቢያዊ የመረጃ መረብ ሥርዓት ያልተፈቀደለት ሰው ሥርዓቱን ሰብሮ መረጃውን ቢያገኘው እንኳን ጉዳት እንዳያደረስብን የሚጠብቅ አማራጭ ነው።
ምሥጢራዊ መረጃ የምንላቸው ባለቤትነታቸው የግለሰብ ወይም የተቋማት የኾኑ በመረጃ መረብ ሥርዓት አልያም በእረፍታ ላይ ያሉ እና ከባለቤቱ ወይም ከተፈቀደለት አካል ውጭ ቢገኝ የፋይናንስ ኪሳራ፣ ክብር እና ዝናን የሚያጎድፉ እና መሰል ችግሮችን ሊያደርስ የሚችልን ይዘት ነው።
ምሥጠራ አራት ዋና ዋና ጥቅሞች ያሉት ሲኾን የመጀመሪያው መረጃ በሚለዋወጡ አካላት መካከል ሰብሮ የሚገባ ያልተፈቀደለት አካል ቢገባ እንኳ ሊረዳው ወደማይችለው ቅርጽ የሚቀይር ስለሆነ ጉዳት እንዳያደርስ ያደርጋል፤ የተላከን መረጃ ለመክፈት ላኪው የሚሰጠን ምስጢራዊ የመክፈቻ ቁልፍ ያለ በመኾኑ የላኪን ትክክለኛ ማንነት እንድናውቅ ያግዛል፤ የመረጃ ምንጩን ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ ሥርዓት ያለው በመኾኑ ሥጋት አይፈጥርብንም፤ ይዘት በሌላ አካል ሊሰረዝ፣ ሊጨመር ወይም ሊቀነስ የሚችልበት መንገድ ባለመኖሩ ያለ ስጋት የመረጃ ልውውጥ ማድረግ ያስችላል። የተላከልን መረጃ የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ስለማይኖርበት የመልእክት ሙሉነት ጉዳይ አሳሳቢ ሊሆንብን አይችልም።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!