
ባሕር ዳር: ሰኔ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በመተማ ከተማ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር መሐመድ ተማም ከዚህ ቀደም የማመርተው ምርት ከራሴ የእለት ፍጆታ አልፎ ለገበያ የሚወጣ አልነበረም ይላሉ፡፡ የሚያመርቱት ምርትም ለገበያ ተፈላጊ አልነበረም፡፡ አርሶ አደሩ ራሳቸውን ለመለወጥ ቀን ከሌሊት ቢታትሩም የሚያገኙት ምርት አነስተኛ ከመኾኑም በላይ ለገበያ ተፈላጊ እንዳልነበረ ያስታውሳሉ፡፡
በዚህም ምክንያት ቤተሰባቸውን ከመመገብ ባለፈ አስፈላጊውን የትምህርት እና መሠረታዊ ወጭዎችን ለመሸፈን ይቸገሩ እንደነበር ነው የሚገልጹት፡። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አርሶ አደሩ በገበያ ተኮር ምርቶች ላይ በመሰማራታቸው ከራሳቸው አልፎ ገበያው የሚፈልገውን ምርት በማምረት ለሌሎችም ማድረስ እንደቻሉ ነግረውናል፡፡
አርሶ አደሩ አስፈላጊ ግብዓቶችን ተጠቅመው ስለሚያመርቱም ውጤቱ የተሻለ እንደኾነም ነው ያብራሩት፡፡ አርሶ አደሩ በዚህ ዓመት የሰሊጥ፣ የአኩሪ አተር እና የማሽላ ምርቶችን አምርተው ለገበያ ለማቅረብ ጥረት እያደረጉ ስለመኾኑ ገልጸው የሰላሙ ሁኔታ ግን ምርታቸውን በሚገባ ማድረስ እንዳልቻሉ አስገንዝበዋል፡፡
ሌላው የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር ጉምቢ ጌታ ለአሚኮ እንዳሉት ገበያ ተኮር ምርቶችን ማምረት ከመጀመራቸው በፊት ይቸገሩ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ ግን ከራሳቸው አልፈው ለገበያው የሚያጠግብ ምርት ማምረታቸውን ነው ያስረዱት፡፡ ባለፈው ዓመት ባመረቱት ምርት መጠቀማቸውን የሚገልጹት አርሶ አደሩ ዘንድሮ የሰሊጥ፣ የአኩሪ አተር እና የማሽላ ምርቶችን በስፋት ማምረት ቢችሉም የጸጥታ ችግሩ ምርታቸውን በሚገባ ለማድረስ ችግር ኾኖባቸው መቆየቱን አስገንዝበዋል፡፡
በዞኑ ገበያ ተኮር ምርቶች በስፋት መመረታቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞን ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ጌታሁን በሪሁን ገልጸዋል፡፡ በ2015/2016 የምርት ዘመን በዞኑ 569 ሺህ 773 ኩንታል ሰሊጥ፣ 587 ሺህ 242 ኩንታል አኩሪ አተር፣ 14 ሺህ 230 ኩንታል ጥጥ መመረቱን መምሪያ ኀላፊው አስረድተዋል፡፡
አቶ ጌታሁን እንደተናገሩት በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ ስጋት ቢኾንም ከክልል እና ከፌዴራል የጸጥታ ዘርፍ ጋር በመነጋገር የግብይት ጊዜያቶችን በማራዘም ለገበያ እንዲቀርቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡ መምሪያ ኀላፊው በዞኑ በ2015/2016 የምርት ዘመን ከተመረተው ገበያ ተኮር ምርት ከስምንት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ስለመገኘቱም ነው የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ፡- ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!