
ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ የ10 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ አካሂዷል። በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ የ10 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የቀጣይ ወራት ዋና ዋና ተግባራትን ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል።
በመድረኩም የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ደኅንነት መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ፣ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ፍስሃ ሀጎስ፣ ከፍተኛ የዞኑ መሪዎች፣ የወረዳ እና ከተማ አሥተዳደሮች እንዲሁም የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የመምሪያው ኀላፊ ፍስሃ ሀጎስ በየደረጃው ያለውን መሪ እና ሙያተኛ ግንዛቤን በማሳደግ በንግድ ተቋሙ የተሻለ ሥራ መሠራቱን ጠቅሰዋል። ኀላፊው በዚህ ዓመት ለውጭ ሀገር ኤክስፖርት የሚኾን 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል። ከዚህ ውስጥ 706 ሺህ 144 ኩንታል ወደ ውጭ መላኩን ተናግረው ከዚህም 74 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስገኝ አስረድተዋል።
ሕጋዊ የንግድ ሥርዓቱን ለማስቀጠል በተደረገው ክትትል እና ቁጥጥር 766 የንግዱ ማኅበረሰብ ፍተሻ የተደረገ መኾኑን አንስተው በዚህም የምርት ጥራት እና ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ ያልነበራቸው ፈቃድ እንዲያወጡ መደረጉን ጠቅሰዋል። በሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ በተወሰደ እርምጃም 13 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ገቢ መደረጉን አንስተዋል።
የንግድ አደረጃጀቱን አቅም በማሳደግ የንግዱ ማኅበረሰብን እና ሸማች ኅብረተሰቡን በግብይት ወቅት የሚገጥሙ ችግሮች እና ጥያቄዎችን በመፍታት አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል በተሠራው ሥራ እስከ አሁን 956 ቅሬታዎች ቀርበው 783 ምላሽ መሰጠቱን ገልጸዋል። በቀጣይ ወራትም ሕገወጥ የንግድ ሥርዓትን በማስወገድ የገበያ ማዕከላትን በማስፋፋት ለንግዱ እና ለሸማቹ ማኅበረሰብ አመቺ የገበያ ልውውጥ እንዲኖር እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
በቂ የሰው ኀይል አለመኖሩ በየጊዜው አየተበራከተ የመጣውን ሕገወጥ ነጋዴ ለመቆጣጠር እና ሥራዎችን ለማከናወን እንቅፋት እንደኾነባቸውም አንስተዋል። አንዳንድ ነጋዴዎች በሸማቹ ማኅበረሰብ ያላግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ መኖራቸውን አንስተው ይህንንም ለመቆጣጠር የገንዘብ እና ሌሎች ቅጣቶች መጣላቸውን ገልጸዋል።
ከዞኑ መንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ እንደተገኘው መረጃ በቀጣይም በንግድ ሥርዓቱ ላይ የተሻለ አገልግሎትን በመዘርጋት በነጋዴዎች እና በሸማቹ ማኅበረሰብ ላይ ሕጋዊ ግብይት እንዲኖር ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!