“በማዕድን ዘርፍ ላይ እሴት ያልተጨመረበት የማዕድን ሃብት ወደ ውጪ እንዳይወጣ የሚል ሕግ እየተረቀቀ ነው” ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ

21

ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ እሴት ተጨምሮባቸው ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡ ማዕድናት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መኾኑን ገልጸዋል። ኢንጅነር ሃብታሙ ተገኝ በኢትዮጵያ የሚገኘው የዓለም የከበሩ ማዕድናት ማኀበርን እና በከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት ጨምሮ ወደ ውጪ የሚልከውን ኦርቢት ኢትዮጵያ የተሰኘ ድርጅት የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል፡፡

የዓለም የከበሩ ማዕድናት ማኀበር በዘርፉ ባለሙያዎችን በማሰልጠን ላይ እንደሚገኝም ተመልክተዋል፡፡ በጉብኝቱ ወቅት የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ የማዕድን ዘርፉ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት እና ለሕብረተሰቡ ኑሮ መሻሻል ያለው አቅም ከፍተኛ ቢኾንም እያበረከተ ያለው ድርሻ ግን አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡

ሀገሪቱ ከማዕድን ዘርፉ ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው በ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ ቅድሚያ ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ መኾኑንም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የሚመረቱ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር እና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

በጉብኝቱ በማዕድን ዘርፉ ላይ የሚሰሩ ሁለት ተቋማትን መጎብኘታቸውን ጠቁመው የሚጠቀሟቸውን ቴክኖሎጂዎች እና የሚያሰለጥኗቸውን የሰው ኃይል መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ የዓለም የከበሩ ማዕድናት ማኀበር በኢትዮጵያ በዘርፉ የሚሰማሩ ሥራ ፈጣሪዎችን በማሰልጠን ላይ መኾኑን ጠቁመው ይህ አንድ ሀገር ማዕድናት ላይ እሴት በመጨምር ለውጪ ገበያ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ የሚያግዝ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

በሌላ መልኩም በዘርፉ ለረጅም ዓመታት የቆየው ኦርቢት ኢትዮጵያ የተባለ ድርጅት ሀገሪቱ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ እንድታገኝ በማድረግ ላይ መኾኑን መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ለትልቅ ብክነት ተዳርጎ የነበረውን የማዕድን ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ሀገር በማዕድን ዘርፍ ላይ እሴት ያልተጨመረበት የማዕድን ሃብት ወደ ውጪ እንዳይወጣ የሚል ሕግ እየተረቀቀ መኺኑንም አስታውቀዋል፡፡ በዘርፉ እሴት ከተጨመረ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ማስገኘት የሚያስችል መኾኑን ጠቁመው እሴት ሳይጨመር ወደ ውጪ እንዳይላክ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

ከዘርፉ ሀገር ማግኘት ያለባትን ገቢ ለማሳደግ የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ ወሳኝ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ በዓለም የከበሩ ማዕድናት ማኀበር የአፍሪካ ዳይሬክተር ሃይማኖት ሲሳይ ማኀበራቸው በኢትዮጵያ በከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት መጨምር የሚችሉ የሰው ሃይልን በማፍራት ላይ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት ያሰለጠኗቸውን 12 ጂሞኖጂስቶችን ለማስመረቅ መዘጋጀታቸውን ጠቁመው ተማሪዎቹ የከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት መጨመር የሚስችላቸውን ስልጠና መውሰዳቸውንም ተናግረዋል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ የሚገኙ የከበሩ ማዕድናት ጥሬውን ወደ ውጪ ከሚላኩ እሴት ተጨምሮባቸው ከፍተኛ ውጪ ምንዛሪ እንዲያስገኙ ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

የኦርቢት ኢትዮጵያ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኀበር ባለቤት እና ሥራ አስኪያጅ ቴዎድሮስ ስንታየሁ በበኩላቸው ድርጅታቸው እሴት በመጨመር እና ወደ ውጭ በመላክ የ15 ዓመት ልምድ ያለው መኾኑን ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ መንግሥት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ገልጸው ዘርፉ በኢንዱስትሪ ደረጃ መሠራት የሚችል እና ለበርካታ ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችል መኾኑን አስታውቀዋል፡፡

ሌሎች ባለሃብቶች በዘርፉ ቢሰማሩ ሀገር ከማዕድን ዘርፍ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ እድል የሚፈጥር መኾኑንም አክለዋል፡፡ በማዕድን ዘርፉ ላይ የሚታዩ ማነቆዎችን ደረጃ በደረጃ በመፍታት ሀገር ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑም ተመላክቷል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት ለተገነባው የዐይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት መዋቅራዊ አደረጃጀት እየተዘጋጀ መኾኑ ተገለጸ፡፡
Next article” ከችግር ለመውጣት ተስማምተን እና አንድ ኾነን መሥራት መቻል አለብን” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ