የአዕምሮ ጤና እና ሌሎች የአካል ክፍሎቻችን ያላቸው ግንኙነት ምንድን ነው?

47

ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአዕምሮ ጤና ዓለም አቀፍ ችግር ሲኾን ከግማሽ በላይ የሚኾነው የዓለም ሕዝብ በሕይወት ዘመኑ ካሉ የአዕምሮ ጤና ችግሮች ውስጥ አንዱን ያስተናግዳል። የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ከሁለት ሰዎች አንዱ በሕይወት ዘመኑ የአዕምሮ ጤና ችግር እንደሚገጥመው ያሳያል።

በዓለም ኢኮኖሚ ፎረም የጤና ጉዳዮች ባለሙያ ዶክተር ሩማ ባርጋቫ አዕምሮ እና ሌላው የሰውነት ክፍል ጥልቅ ቁርኝት ያላቸው በመኾኑ ሁለቱንም በአንድ ላይ መንከባከብ እና መጠበቅ ለጤንነታችን ጠቃሚ ነው ይላሉ። የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም የአዕምሮ ጤና ግንዛቤ መፍጠሪያ ወርን አስመልክቶ ባወጣው ጽሑፍ የአዕምሮ እና ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ያላቸውን ግንኙነት ለማብራራት በጭንቀት ጊዜ ሆድ አካባቢ የሚፈጠርን የሚረብሽ ስሜት እና በፍርሃት ጊዜ የልብ አብዝቶ መምታትን እንደ ቀላል ማሳያ ያነሳል።

ሀሳባችን እና ሰውነታችን ላይ የሚሰማን ስሜት የተሳሰረ እንጂ የተነጣጠለ አለመኾኑን እና አዕምሯችንን ከሌሎች የሰውነታችን ክፍሎች ነጣጥሎ ማየት ስህተት መኾኑን ዶክተር ሩማ በርጋቫ ተናግረዋል። እንደ ዶክተር ባርጋቫ ገለጻ ጭንቀት እና ፍርሃት በአካል ክፍሎቻችን ላይ ተጽዕኖን ይፈጥራሉ። ጭንቀት እና ፍርሃት በአካላችን ላይ የሚገለጥ ችግርን ያመጣሉ። የሰውነታችን ሙቀት እንዲጨምር፣ የመንቀጥቀጥ ስሜት እንዲሰማን ያደርጉናል።

እንዲህ አይነት ምልክቶች የአዕምሮ እና የሰውነት ክፍሎቻችን ያላቸውን ቁርኝት ለማሳየት የሚያስችሉ ቀላል አብነቶች ናቸው። የአካል ክፍሎቻችን ከአዕምሯችን ጋር ስላላቸው ቁርኝት ያለው ዕውነት አሁን የታወቀ ሳይኾን ከ2ሺህ 500 ዓመታት በፊት የተለየ መኾኑን እና ታሪካዊ የሕክምና ንድፈ ሃሳቦችም የሚያረጋግጡት መኾኑን ጹሑፉ ያስረዳል።

ጹሑፉ ዋቢ ባደረገው ጥናት በወንዶች እና ሴቶች በሕይወት የመቆየት ምጣኔ ላይ ያለው ተጽዕኖ ተመላክቷል። 30 ዓመት እድሜ ያላቸውን ሰዎች ባካተተ ጥናት መሠረት ከባድ ጭንቀት የወንዶችን በሕይወት የመቆየት ምጣኔ በ2 ነጥብ 8 ዓመት እና የሴቶችን ደግሞ በ 2 ነጥብ 3 ዓመት የሚቀንስ መኾኑ ተመላክቷል ።

በመኾኑም ይህን እውነታ አዕምሯችን እና የሰውነት ክፍሎቻችን ያላቸውን የተቆራኘ ግንኙነት እንድንረዳ፣ ጤናማ እና ደስተኛ ሕይወት እንድንኖር ያግዘናል። ዶክተር ባርጋቫ ድባቴ እና ፍርሃት ምርታማነትን በመቀነስ በምጣኔ ሃብት ላይ ትልቅ ኪሳራን እንደሚያደርሱ ገልጸዋል። እነዚህ ሁለቱ የአዕምሮ ጤና ችግሮች በየዓመቱ አንድ ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ እንዲደርስ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያዊን አጀንዳዎቻቸውን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማቅረብ በውይይት እንዲፈቱ ማድረግ አለባቸው” አስቻለ አላምሬ
Next articleበቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት ለተገነባው የዐይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት መዋቅራዊ አደረጃጀት እየተዘጋጀ መኾኑ ተገለጸ፡፡