
ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ “የገበያ ማዕከላትን በማስፋፋት እና በተዋንያን መካከል ትስስር በመፍጠር የተሳለጠ ግብይት እንገነባለን” በሚል መሪ መልዕክት ለጅምላ ነጋዴዎች እና ሸማች ማኀበራት ሥልጠና ሰጥቷል፡፡
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኅላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር) ንግድ እና ገበያ ልማትን በቴክኖሎጅ የማስደገፍ ልምድ ደካማ እንደነበር ጠቅሰዋል። ይህም በሀገር ውስጥም ኾነ በወጭ የግብይት ሥርዓቱ ላይ ከፍተት ፈጥሮ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡
የክልሉ ንግድ እና ገበያ ውጤታማ እንዲኾን ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አብረው የሚጓዙ አዳዲስ አሠራሮች ላይ ግንዛቤ መፍጠር ፣ በረጅሙ የግብይት ሰንሰለት ውስጥ ደላላው ስለሚበዛ ሳይንሳዊ የኾነ የግብይት ትስስር መፍጠር እና የገበያ መረጃ ሥርዓት መዘርጋት በትኩረት የሚሠራባቸው ጉዳዮች እንደኾኑ ገልጸዋል፡፡
የግብይት ሥርዓቱን ጤናማ ለማድረግም አዳዲስ ቴክኖሎጀዎችን ለመጠቀም በሂደት ላይ መኾናቸውን አንስተዋል፡፡
አንዳንድ ከተሞች ሸማቹ ማኅበረሰብ በቀጥታ የሚገበያይበትን ሥርዓት መተግበር መጀመራችው በሥልጠናው በመልካም ጎኑ ተነስቷል፡፡
የሥልጠናው ተሳታፊዎችም ተግበሩን ለማሳለጥ እና እየተስተዋለ ያለውን በደላላ የተወሳሰበ የግብይት ሥርዓት እንዲሻሻል ለማድረግ እንሠራለን ብለዋል፡፡
ደጀን አምባቸው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!