ጤና ሚኒስቴር እና ግሎባል ፈንድ ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

11

ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጤና ሚኒስቴር እና ግሎባል ፈንድ ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ የድጋፍ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ድጋፉ የቲቪ፣ የኤች አይ ቪ እና የወባ በሽታዎችን መቆጣጠር የሚያስችል ነው ተብሏል።

ስምምነቱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና በግሎባል ፈንድ የአፍሪካ ዲፓርትመንት ኅላፊ ሊንዶን ሞሪሰን ፈርመውታል፡፡

በግሎባል ፈንድ የአፍሪካ ዲፓርትመንት ኅላፊ ሊንዶን ሞሪሰን ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ለ2030 ያስቀመጣቸውን የጤና ግቦች ቀድማ እያሳካች ትገኛለች ብለዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ የቲቪ፣ የኤች አይ ቪ እና የወባ በሽታዎችን ለመቆጣጠር ከግሎባል ፈንድ ጋር በትብብር መሥራት ከጀመረች ሁለት አሥርት ዓመታትን አስቆጥራለች ብለዋል፡፡

በዚህም ግሎባል ፈንድ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የቲቪ፣ የኤች አይ ቪን እና የወባ በሽታዎችን ለመቆጣጠር እና አጠቃላይ የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል የ3 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡

ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በተከናወኑ የጋራ ጥረቶች ስኬቶች መመዝገባቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሯ አሁንም የሚቀሩ ሥራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ስምምነቱ የቲቪ፣ የኤች አይ ቪ እና የወባ በሽታዎችን ሥርጭት ለመቆጣጠር ለሚከናወነው ሥራ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መኾኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ ስምምነቱ ከ2017 በጀት ዓመት ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት የሚተገበር ፕሮጀክትን ያካተተ ነው፡፡ በዚህም የጤና ባለሙያዎችን ከማሠልጠን እና የጤና ተቋማትን ከመገንባት ባሻገር የመድኃኒት አቅርቦትን ለማጠናከር እንደሚውል ተጠቁሟል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በበጀት ዓመቱ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ጥራት ያለው የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ነው” ሙፈሪሃት ካሚል
Next articleየንግድ ሥርዓቱን ጤናማ እና የተሳለጠ ለማድርግ እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡