
ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ዘሚ ዘሚ” አለቻት ዝም በይ ዝም በይ ማለቷ ነበር፤ ፈስሳ እንዳታልቅባት፡፡ እውነቷን ነው በልመና የተገኘች፣ በሀሩር መካከል የፈለቀች እና ነፍስ አድን ሰማያዊ የአሏህ ስጦታ ናት፡፡
የሕጻንን ነፍስ ለመታደግ እና የእናትን አንጀት ለማራስ የፈለቀች የሕይዎት ውኃ ነች፤ የዘምዘም ውኃ፡፡ ሃጀር ዘሚ ዘሚ ባትላት ኖሮ የዘምዘም ውኃ ምንኛ ዓለምን ባጥለቀለቀች ነበር፡፡ ዳሩ ከሕግ እና ከወሰን፤ ከልክ እና ከመጠን እንዳታልፍ ዘሚ ዘሚ ተባለች።
ይኽው ዛሬ የሚጠጣት ባይኖር ሞልታ አትፈስስም፤ የሚጠጣት ቢበዛ ምንጯ አይደርቅም፡፡ ከዓለም ዙሪያ ሀጂ የሚያደርግ ሙስሊም ጠጥቷት እና ቀድቶ ወደ የሀገሩ ወስዷት የዘምዘም ውኃ ዛሬም ድረስ ከልክ አታልፍም፤ ከወሰኗም አትጎድልም፡፡
የዘምዘም ውኃ የእናት ጥረት የልጅ ጩኽት ያፈለቃት ልዩ ስጦታ ናት፡፡ ዛሬ ከመላው ዓለም የሚመጡ ሙስሊሞች ሊቀምሷት የሚጓጉላት እና በሕይዎት ዘመናቸው ሊጎበኟት የሚሿትን የዘምዘም ውኃ ያኔ በምድረ በዳ ብቻቸውን የነበሩት እናት እና ልጅ አጥብቀው ፈልገዋት ነበር፡፡ የዘምዘም ውኃ የአሏህ እዝነት እና የመላዒካ ተራዳዒነት የተስተዋለባት የሕይዎት ውኃ ናት፡፡
ሃጀር ከባለቤቷ ኢብራሂም ተለይታ በምድረ በዳ ውስጥ ብቻዋን ስትቀር ተስፋ ያደረገችው ፈጣሪዋን ነበር፡፡ የሕጻኑን ኢስማኤልን ነፍስ የሚታደግ ጠብታ ውኃ ለማግኘት ያንን ሰንሰለታማ ተራራ ሰባት ጊዜ ወጥታ ሰባት ጊዜ ወርዳበታለች፡፡
የልጇን እስትንፋስ የሚያቆይ ጠብታ ውኃ አጥታ የምትብከነከነው እናት ሃጀር ብቸኛ ረዳቷ ከሰማይ እንደኾነ ብታምንም ምድር ተዓምር ታሳያት ዘንድ ደጋግማ ማስናባታለች፡፡ የሶፋ እና የመርዋ ኮረብታማ ተራራዎች የኢስማኤልን ነፍስያ እንዲያቆዩላት ደጋግማ ተማጽናቸዋለች፡፡
የልጇን ምርር ያለ ለቅሶ ሰምታ አንጀቷ በሃዘን የተላወሰባት ሃጀር በመጨረሻም በመረዋ ተራራ ላይ ሳለች ድምጽ ወደ ጆሮዋ የመጣ መሰላት፡፡ ለሰባተኛ ጊዜ በመርዋ ተራራ ላይ ሳለች የሰማችውን ድምጽ አቅጣጫ ለማረጋገጥ ለራሷ “እሽሽ…እሽሽ…” አለችና ድምጹን የሰማችበት ወደ መሰላት አቅጣጫ ጆሮዎቿን አቀናች፡፡
የሰማችው ድምጽ ግን አልተደገመም፤ ፀሐይ ያለገደብ በምትንቀለቀልበት በዚያ ምድረ በዳም ለዐይኖቿ እንግዳ ነገር አልተስተዋለም፡፡ ከቀደመው ሁሉ አሁን ነፍስያዋ ልትወጣ የቀረበች በሚመስል መልኩ ትንፋሿን ሳይቀር ውጣ አዲስ ነገር ትጠብቃለች፤ ግን ጠብ ያለም ብቅ ያለም ነገር አላየችም፡፡
እናት ሃጀር በሞት እና በሕይዎት መካከል ቆማ ተስፋ ያደረገችውን ፈጣሪ የመጨረሻ ልመና አሰማች፡፡ “የሆነ ድምጽ ሰምቻለሁ… ረጂ ከኾንክ እባክህን ድረስልኝ…እርዳኝ” አለች፡፡ መልስ ስታጣ ልጇን ወዳስቀመጠችበት አቅጣጫ ዘወር አለች፡፡
በዚያ ስፍራ አንድ መልአክ በክንፎቹ መሬት ሲቆፍር ተመለከተች፡፡ መልአኩም ውኃው ከመሬቱ እስኪፈልቅ ድረስ በክንፎቹ እየቆፈረው መኾኑን ተመለከተች፡፡ የሕይዎት ምንጭ ከኾነችው የዘምዘም ውኃ ቀድማ በደስታ ጎርፍ የተጥለቀለቀችው ሃጀር ወደ ሕይዎት ውኃ ፈጠነች፡፡
ሃጀር በስንት ልመና እና ለቅሶ ያገኘችው የሕይዎት ውኃ ፈስሶ እንዳያልቅባትም በአፈር እና ድንጋይ ገደበችው፡፡ የዘምዘም ውኃ የሚለው ስያሜ የተገኘው ከዚሁ ከመገደቧ ጋር ተያይዞ ነው ያሉን የእስልምና አስተምህሮ መምህሩ ሸክ አብዱራሂም ሙሳ ሃጀር ውኃዋ ከፈለቀችላት በኋላ “ዘሚ ዘሚ” አለቻት እንዳታልቅባት ዝም በይ ዝም በይ ስትል መድፈኗ ነበር ይሉናል፡፡
ማንኛውም ውኃ ጥምን ሊያረካ ይችላል የሚሉት ሸክ አብዱራሂማን የዘምዘምን ውኃ የተለየች የሚያደርጋት ግን እንደ ምግብም የምታጠግብ ጭምር መኾኗ ነው ይላሉ፡፡
በዚያ የደስታ ማዕበል ውስጥም እንኳን ኾና ሃጀር ብርቱ ናት፤ ለቀጣይም ታስባለች እና የተሰጣትን የሕይዎት ውኃ ጠበቀች፡፡ ሃጀር የትዕግስቷን ጥፍጥና ለልጇ አቀመሰች፡፡
ባሮቹን በሚያክመው ወዳጆቹን በሚሸልመው፤ ፍጥረቱን በማይረሳ የወደቁትን በሚያነሳ ፈጣሪዋ ስለትዕግስቷ፣ ስለፅናቷ እና ስለድካሟ “የዘምዘም ውኃ” ተሰጣት፡፡
በዚያ ምድረ በዳ ሕይዎት የሚታደግ የሕይዎት ውኃ ፈልቆላት የልጇን ጥም አረካች፤ እርሷም ተጎነጨች፡፡ የዘምዘም ውኃ በሃጀር ዘሚ ዘሚ ባትባል ኖሮ ዓለም ምን ይውጣት ነበር ብሎ ማሰብም ያስፈልጋል፡፡
ስትሞላ ራሷ የምትቆም ከተመደበው በላይ የማታመነጭ እና በቀን 691 ሚሊዮን ሊትር የምትሰጥ ናት፡፡ የዘምዘም ውኃ ትናንት ምድረ በዳ ውስጥ ብቻቸውን ለነበሩት ዘምዘም እና ኢስማኤል ብቻ የተሰጠች አይደለችም፡፡ የዘምዘም ውኃን ዛሬም ድረስ በዓለም ዙሪያ ያሉ መስሊሞች ለፈውስ የሚቀምሷት የበረካ ውኃ ነች፡፡
ናሽናል ላይብረሪ ኦቭ ሜዲሲን “የዘምዘም ውኃ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚገቡ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ አማኞች በብዛት የሚፈልጉት ውኃ ነው” ይላል፡፡ ለዓረፋ በዓል በአካባቢው የመታደም ዕድል ያገኙ ሙስሊሞች ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ለቅርብ ወዳጆቻቸው፣ ዘመዶቻቸው እና ጓደኞቻቸው የዘምዘም ውኃን ስጦታ አድርገው ይወስዳሉ።
የዘምዘም ውኃ ለፈውስ የሚውል እና ሃይማኖታዊ ቅቡልነቱ የላቀ ውኃ ስለመኾኑም አንድ ወቅት ቢቢሲ በሠራው ዶክመንታሪ ላይ ያነጋገራቸው የሃይማኖቱ ሰዎች ይገልጻሉ፡፡
የዘምዘም ውኃ ካንሰርን ጨምሮ በርካታ የጤና ችግሮችን ለመከላከል የሚያስችል ንጥረ ነገር እንዳለውም ይታመናል ይላል፡፡ የዘምዘም ውኃ በሁሉም ኢስላማዊ እና አረብ ሀገራት ዘንድ ካሉ የውኃ ምንጮች ሁሉ የተለየ እና ተመራጭ ንጹህ ውኃ ስለመኾኑ ናሽናል ላይብረሪ ኦቭ ሜዲሲን ያትታል፡፡
የእናትን ጥረት እና የልጅን ጩኽት ሰምቶ ፈጣሪ በምድረ በዳ መካከል ያፈለቀው የሕይዎት ውኃ ከሃይማኖት አልፎ ሳይንስ ሳይቀር ተመራጭነቱን ያረጋግጣል፡፡ ቢቢሲ በዘገባው በዘምዘም ውኃ ዙሪያ ፍሬያማ ምርምሮች መደረጋቸውን ጠቅሶ ከብክለት የጸዳ፣ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን የያዘ እና ከመጠጥ አልፎ ለፈውስ አገልግሎት የሚውል ውኃ ነው ይላል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!