
ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አንድ ወቅት ምድረ በዳ የነበረችው ቅድስቲቷ ምድር መካ የአሏህ ክብር እና ፍቅር ተገልጦባት ሁልጊዜም በየዓመቱ በሚሊየን በሚቆጠሩ የሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ትዘየራለች፡፡
ሰማዩን እንደ አዕዋፍት ከሰው በላይ ከፍ ብለው እየቃኙ በሚያስመለክቱን የካሜራ ምስሎች ስንመለከተው ካባን የከበበው የበረዶ ክምር እንጂ የሰው ዘር አይመስልም ነበር፡፡
ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ኢስማኤልን እና ባለቤታቸውን ሃጀር ይዘው ያደረጉትን የበርሃ ጉዞ 632 ዓ.ም ላይ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ዳግም ተጓዙት፡፡ የሀጂ ሥርዓት በዚህ መልኩ ተጀመረ፡፡
በዓረፋ በዓል የሀጂ ሥርዓትን ለመፈጸም ወደ ቅድስቲቱ ምድር መካ መዲና የሚጓዙ የሃይማኖቱ ተከታዮች በቆይታቸው የተለያዩ ቦታዎችን ይጎበኛሉ፡፡ ከመካ ወደ መዲና፣ ከዓረፋ ወደ ሙዝደሊፋ፣ ከሚና ወደ ጀማረፋት፣ ከሚና ወደ መካ እየተንቀሳቀሱ ምስጋና ያቀርባሉ፡፡
የዘር ሃረግ፣ የቆዳ ቀለም፣ ምጣኔ ሃብታዊ ደረጃ፣ የመደብ ልዩነት እና ሥልጣን ሳይገድባቸው በአሏህ ፊት እኩል የሚኾኑበት ሥርዓት ነው፤ የሀጂ ሥርዓት፡፡
ከሁሉም የዓለም ክፍሎች የተሰባሰቡት አማኞች በዚያች ቅድስት ከተማ ከቅዱስ ተግባራት እና ምስጋና ውጭ ከአፋቸው እንኳን ክፉ አይወጣም፡፡ ያሰባሰባቸው የአሏህ እዝነት እና ርህራሄ ነውና “አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ” ከመባባል ያለፈ ክፉ ነገር ፈጽሞ የለም፡፡
በሚሊየን የሚቆጠሩ አማኞች በሚሰባሰቡባት በዚያች ጠበባ የካባ ሥፍራ ለሰላት እንኳን በአንድ ጥሪ ብቻ ቦታ ቦታቸውን ይዘው ለስግደት ይዘጋጃሉ፡፡
በዒድ አል አድሃ በዓል ከሚፈጸሙ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች መካከል አንዱ ሀጂ ማድረግ ነው፡፡ አንድ ወቅት የሀጂ ሥርዓት ሃይማኖታዊ ምክንያቱ ምንድን ነው? ስንል የሀጀጁ አንድ የሃይማኖቱን አስተማሪ አነጋግረን ነበር፡፡
ሀጂ ማድረግ የእስልምና ሃይማኖት ከቆመባቸው አምስት ምሰሶዎች መካከል አንዱ ነው ያሉን ሼህ አብዱራሂም ሙሳ ናቸው፡፡ አንድ ሙስሊም በሕይዎት ዘመኑ ሊያሳካቸው ከሚፈልጋቸው ሃይማኖታዊ ምኞቶች መካከል ቀዳሚው ሀጂ ማድረግ ነው ይላሉ፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ሀጂ ሳደርግ የተሰማኝን የደስታ ስሜት ያክል ደስታን አጣጥሜ አላውቅም የሚሉት ሼህ አብዱራሂም በቁራኣን የተማርናቸውን፣ በሃይማኖት አስተምህሮ መጻሕፍት ያነበብናቸውን እና ከታላላቆቻችን የሰማናቸውን ቅዱስ ቦታዎች መመልከት የተለየ ስሜት ይሰጣል ይላሉ፡፡
የሀጂ ሥርዓት ዓለም ስለእኩልነት ልትማርበት የሚያገባ ጠቃሚ እና ገንቢ እሴቶች ያሉት ነው የሚሉት ሼህ አብዱራሂም መከባበሩ፣ መቻቻሉ እና አንድነቱ ፍጹም የተለየ ስሜትን የሚሰጥ ነው ይላሉ፡፡
“ሀጂ ማድረግ በምድር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነባችውን የአሏህን ቤት መጎብኘት ነው” የሚሉት ሼህ አብዱራሂም ካእባን ሰባት ጊዜ ሙሉ እየዞሩ ማመስገን ምን ዓይነት የደስታ ስሜት ይፈጥራል ብትለኝ መግለጽ ይከብዳል ይላሉ፡፡
ከነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጉዞ በኋላ አካላዊ አቅማቸው፣ ጤንነታቸው እና የገንዘብ አቅሙ የፈቀደላቸው ሃይማኖቱ ተከታዮች ሁሉ በሕይዎት ዘመናቸው አንድ ጊዜ ሀጂ እንዲያደርጉ ያስገድዳልም ይላሉ፡፡
በመካ በሚገኘው ታላቁ መስጂድ እምብርት ላይ ያለው ጥቁር ሀር ለበስ ካባ በነቢዩ ኢብራሁም እና በልጃቸው እስማኤል የተገነባ ነው። በዚህ መስጂድ ዙሪያ ያለው የሀጃጆች ውበት እና ሙሃባ የተለየ ነው፡፡
ሀጂ የልዩነትን በር አጥብቦ የአንድነትን፣ የመተሳሰብን እና የአብሮነትን መንገድ የሚከፍት ነው የሚሉት ሼህ አብዱራሂም የሀጅ ዋና ዓላማውም አንድነትን ማጽናት ነው ብለዋል፡፡
ሀጅ አስተምህሮው ጠሊቅ፣ ምሥጢሩ ረቂቅ እና ፋይዳው ትልቅ ነው የሚሉት ሼህ አብዱራሂም እኛ የአሏህ እንግዶች ነን፤ የአሏህ እንግዶች ደግሞ የፈጣሪያቸውን ቤት መጎብኘታቸው ብዙ እንዲያተርፉ ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡ እኔ በመሀጀጄ ብዙ ብዙ አትርፌያለሁ፤ ሌሎችም ያ ሙሃባ እንዲደርሳቸው እመኛለሁ ብለውን ነበር፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!