“አንድነት የሚጸናበት፤ ለአንድ ፈጣሪ የሚሰገድበት”

22

ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ)መለያየትን ይረሳሉ፣ ዘርና ቋንቋን ይዘነጋሉ፣ ሃብት ይተዋሉ፣ ጌታና ሎሌ በአንድነት ይቆማሉ፣ ንጉሥ እና አገልጋይ እኩል ይታያሉ፣ ንግሥት እና ደንገጡር በእኩልነት ይቆማሉ፣ በዚያ ሥፍራ ንጉሥ ከአገልጋዩ ልቆ አይዋብም፣ ንግሥት ከደንገጡሯ አምራ አትታይም፣ በዚያ ሥፍራ ባለጸጋ ከደሃው አይበልጥም፣ ነጭም ጥቁርም አይለያይም፣ በዚያ ሥፍራ ሰልፍ የሚበዛላቸው፣ የእጅ መንሻ የሚቀርብላቸው፣ ከጧት እስከማታ ሽቱ የሚርከፈከፍላቸው ከሌሎች አይበልጡም ሁሉም በአንድነት ይጸናሉ፣ በአንድነትም ይቆማሉ፣ ለአንድ ፈጣሪም ይሰግዳሉ እንጂ።

በቋንቋ የማይግባቡት፣ በነገድ የሚለያዩት፣ በቀለም የማይገናኙት፣ በሀገር ተለያይተው የሚኖሩት፣ በሰሜንም በደቡብም፣ በምሥራቅም በምዕራብም የሚኖሩት በአንድነት ይገናኛሉ። ከየት መጣህ አይባባሉም፣ በዐይናቸው ተያይተው፣ በልባቸው ይግባባሉ፣ በፍቅር ይዘያየራሉ፣ በልባቸው ፈጣሪያቸውን ያስባሉ፣ በረከትን ይቀበላሉ፣ ፈጣሪያቸው እዝነትን ያደርግላቸው ዘንድ ይበረታሉ።

እንደዛሬው አየር በሰማይ በማይበርበት፣ መኪና በምድር በማይሽከረከርበት፣ ባሕር የሚከፍሉ ዘመናዊ ጀልባዎች ባልተሠሩበት፣ እሾህና አሜካላ በበዛበት፣ ረሃብና ጥም ባየለበት፣ የሚያቃጥል በረሃ በጠነከረበት፣ በበረሃው እባቡና ጊንጡ በሚናደፍበት፣ ለዐይን ማረፊያ የሚኾን ልምላሜ በማይታይበት፣ የተጠማችን ጉሮሮ የምታርስ ጥቂት የምንጭ ውኃ በማትፈስስበት፣ የደከመው የሚያርፍባቸው፣ የተራበ የሚጎርስባቸው በየመንገዱ ጎጆ ባልተቀለሱበት፣ ከላይም ከታችም በረሃ በሚናደፍበት፣ በዙሪያ ገባው ሞት በሚያንዣብብበት፣ ለእግራቸው ጫማ በማይጫሙበት በጥንት ዘመን ጀምሮ ከአሏህ ዘንድ በረክትን ይቀበሉ ዘንድ የወደዱ ሙስሊሞች መከራውን ችለው ወደ ተቀደሰው ሠፍራ ይገሰግሳሉ።

በዚያ ሥፍራ የነብያት ሁሉ አባት ነብዩ ኢብራሂም መስዋዕት አቅርበውበታል፣ ከልጅ ፍቅር ይልቅ የፈጣሪያቸውን ፍቅር አስበልጠውበታል፣ በትሕትና ታዝዘውበታል፣ ፈተና ተፈትነው ከክብር ላይ ክብር ደርበው አልፈውበታል፣ አሏህ የላካቸው ነብይ ነብዩ ሙሐመድ የመጨረሻውን ትምህርት አስተምረውበታል፣ ሕግ እና ሥርዓት ይጸና ዘንድ አዝዘውበታልና በረከት የመላበት፣ የፈጣሪ እዝነት የሚገኝበት ነው።

የዓለም ሙስሊሞች በሃይማኖት ከተቀደሱት ተራራዎች ሁሉ ወደ ተቀደሰው ተራራ ይጓዛሉ። በምድር የተዘሩ ከዋክብት መስለው ባዘቶ የመሰለ ነጭ ልብስ ለብሰው ይገሰግሳሉ፣ በዚያ በተዋበ እና ባማረ ተራራ ላይ ነጭ ለብሰው ይሠባሠባሉ። በዚያ ጊዜ የተቀደሰው ምድር ነጭ በለበሱ አማኞች ይመላል፣ እጅግ አብዝቶ ይዋባል። ይህ የተቀደሰ ተራራ አረፋ ይሰኛል። የዒድ አል አደሃ ዓረፋ በዓል በታሰበ ቁጥር ስለዚህ ቅዱስ ተራራ ይነገራል። ዒድ አል አደሃ ዓረፋ የሀጂ ሥርዓት የሚተገበርበት፣ ከእስልምና መሰሶዎች መካከል አንደኛው ነው።

ዓረፋ ከሰው ልጆች አባት እና እናት ከአደም እና ከሐዋ ጋር ይገናኛል ይላሉ። አደም እና ሐዋ በጀነት ሳሉ ተሳስተው በደሉ። በበደሉም ጊዜ ከጀነት ወጡ። ከጀነት እንደወጡም ተጠፋፍተው ነበር። ከብዙ ጊዜ በኋላም በተዋበ ተራራ ላይ ተገናኙ። በተገናኙም ጊዜ አረፍትኒ አወቅሽኝን ሐዋ አረፍከኒ አደም አወከኝን አደም? አንተ ማነህ? አነ አደም እኔ አደም ነኝ። አንቺ ማነሽ ? ሐዋ ነኝ። ከዚህም ተዋወቁ። ተገናኝተው ተደሰቱ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያቺ ተራራ አረፋ ተባለች ይላሉ። በዚህም ቀን ኢስላሞች ነሸዳውን ይበሉ፣ ዱዓውን ያድርሱ፣ ምሥጋናውን ያቀርቡ ተብሎ ታዝዟል።

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ ሙሐመድ አንዋር የዒድ አል አደሃ ዓረፋ በዓል ሁለት ዓይነት አነሳስ አለው ይላሉ።

የመጀመሪያው ከአደም ዘመን ጀምሮ ሲከበር የነበረ፣ እስካሁንም ድረስ የቀጠለ ነው። በሁለተኛ ደግሞ የነብያቶች ሁሉ አባት ነብዩ ኢብራሂም ጋር ይጠቀሳል። እርሳቸው በአሏህ ዘንድ የተመረጡ ናቸው፣ የአሏህን አንድነትም ያስተጋቡ ታላቅ ነብይ ናቸው። እሳቸውን አሏህ ወንድ ልጅን ሰጣቸው። የሚወዱት የሚሳሱለት ልጅ አጎናጸፋቸው።

ከዚህም በኋላ የፈተና ጊዜም መጣባቸው። ትዕዛዝ ከአሏህ ዘንድ መጣ። ልጅህን ለመስዋዕትነት አቅርብ የሚል ትዕዛዝ። የልጃቸው መውደድ ጸንቶባቸው አባትነት ፍቅር ነው የሚያስቀድሙ ወይንስ የአሏህን ፍቅር ያስቀድማሉ የሚል መንታ መንገድ ላይ የሚያስቆም ታላቅ ፈተና ቀረበላቸው። እሳቸውም የአላህን ፍቅር አስቀድመው ፈተናውን ተወጡ። ልጃቸውን ለመስዋዕትነት አቀረቡ።

ልጃቸውንም ለመስዋዕትነት አቅርበው የቢላዋውን ስለት በልጃቸው አንገት ላይ ባስቀመጡበት ጊዜ በመላእክት አማካኝነት ከአሏህ ዘንድ ጥሪ መጣ። በልጁ ፈንታ መስዋዕት ሊኾን የሚችል በግ ከሰማይ ወረደ ይላሉ ስለ ዒድ አል አደሃ ዓረፋ በዓል ሲናገሩ። ዓረፋም የመስዋዕትነት፣ የመታዘዝ ቀን እየተባለ ይከበራል።

ይህ በዓል ከአሏህ ዘንድ የሚመጣን ማንኛውም ትዕዛዝ ሳናቅማማ፣ በየትኛውም ቦታ፣ በየትኛውም ሁኔታ ኾኖ መፈጸም እንደሚገባ ያስተምራል። ልጅህን ረድ ከሚል የበለጠ ታላቅ ፈተና የለም። ነብዩ ኢብራሂም ግን ያንን ፈተና አለፉት። የልጁ ትዕዛዝ አክባሪነትም ባየ ጊዜ ልጆች ለአሏህ፣ ከዚያም ለአባታቸው ታዛዥ መኾን እንዳለባቸው ያስረዳል ነው የሚሉት።

ከአሏህ ትዕዛዝ መጥቷልና እኔ አርድሀለሁ ባሉት ጊዜ ልጁም አባዬ ኾይ የታዘዝከውን ነገር በእኔ ላይ ፈጽም፣ በአሏህ ፈቃድ ከታጋሾቹ ኾኜ ታገኘኛለህ። የአሏህ ትዕዛዝ እስከኾነ ድረስ እኔን ለምን ታርደኛለህ ብዬ አላቅማም አለ ይላሉ።

እንደ ሼሁ ገለጻ ለሰው ልጆች ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነባው የአምልኮ ስፍራ የሙስሊሞች የሶላት አቅጣጫ ካዕባው ነው። ለሰው ልጆች ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነባው ያ በቅድስቷ ከተማ መካ ያለው ቤት ነው። እዛ ውስጥ የአሏህ ታዕምር አለ።

ነብዩ ኢብራሂም የአሏህን ቤት ካዕባን በሚሠሩበት ጊዜ የቆሙበት ድንጋይ አለ። ይህም በአሏህ ፈቃድ ወደላይ ከፍ እያደረጋቸው፣ ወደ ጎንም እየወሰዳቸው የአሏህ ቤት በተዓምር ተሠራ። የአሏህ ቤት ከነብዩ ኢብራሂም አስቀድሞ በሰው ልጆች አባት አደም ጊዜ የተሠራ ነበር። ነገር ግን የኖህ ዘመን የጎርፍ ጥፋት በመጣ ጊዜ አሏህ በመላእክት አማካኝነት ወደ ሰማይ እንዲያርግ አደረገው። እስከ ነብዩ ኢብራሂም መምጫ ዘመንም ቦታው ብቻ ቅዱስ ኾኖ ኖረ።

ነብዩ ኢብራሂም በመጡ ጊዜም ለዘመናት ምድረ በዳ ኾኖ በቆዬው ቅዱስ ሥፍራ በአሏህ ትዕዛዝ አማካኝነት ልጃቸውን እና ባለቤታቸውን ያስቀመጡበት ሥፍራ ነው። በዚህም ሥፍራ በአሏህ ትዕዛዝ አማካኝነት የአሏህ ቤት ካዕባ ተገነባ። የመጀመሪያ በመላእክት የተሠራ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ በነብዩ ኢብራሂም አማካኝነት የተገነባ ነው። ነብዩ ኢብራሂም የአሏህን ቤት ገንብተው ከጨረሱ በኋላ አሏህ ትዕዛዝ አስተላለፈ። ሕዝብን ሁሉ፣ አማኝን ሁሉ ይሄን የገነባሁትን ቤት እዩ ብለህ አዋጅን አውጅ አላቸው። ነብዩ ኢብራሂምም አሏህ ኾይ እንዴት ኾኖ ይኾናል የኔ ጥሪ ከዚህ ተራራ የማያልፍ ነው። ድምጼ ድንበር ተሻጋሪ አይደለም። ታዲያ እንዴት ኾኖ እጣራለሁ? አሉ።

አሏህም ጥሪውን የማስተላልፈው እኔ ነኝ። አንተ ግን ይሄን አንድነትን ጥሪ የምትጣራው ትዕዛዙን ለመፈጸም ነው አላቸው። እሳቸውም ትዕዛዙን ፈጸሙ። ከዚያም ጊዜ ጀምሮ አማኞች የአንድነት መገለጫ ወደ ኾነው የሀጂ አምልኮ ይተማሉ።

ሀጂም ታላቅ ኢባዳ ነው። ሀጂ የአንድነት መገለጫ ነው። ሁሉም አንድ ዓይነት ልብስ ለብሶ በአንድ ቦታ ላይ በአንድ ተራራ ላይ ተሠባሥቦ የአሏህን እምነት የሚያስተላልፍበት ነው ይላሉ። በዚህ ሥፍራ ሁሉም እኩል ነው እንጂ የተለየ ክብር የሚሰጠው፣ የተለየ ምንጣፍ የሚነጠፍለት፣ የተለየ ክብር የሚደረግለት የለም። ሁሉም በአሏህ ፊት እኩል እንደኾነ ሁሉ በዚያም ሥፍራ እኩል ኾነው ይቆማሉ።

በዚህ ሥፍራ ኃያልነት ለአሏህ ብቻ እንጂ ዘርን፣ ብሔርን፣ ቀለምን፣ ቋንቋን፣ ሀገርን መሠረት ያደረገ ኃይል የለም እያሉ ይሠባሠባሉ። ይህንም አንድነት የሰው ልጆች ሁሉ ሊያደርጉት የተገባ ነው። ይህን ካደረጉ የዓለም ችግር ሁሉ ይቀረፋል።

ይህ ሥፍራ የሰው ልጅ እንዳይኮራ፣ ባለ ጸጋ ነኝ፣ ባለሥልጣን ነኝ፣ የሞላልኝ ነኝ እንዳይል፣ ሞትን እንዲያስብ ያስተምራል ነው የሚሉት ሼሁ። መነሳትን ያስታውሳል። ከአሏህ ፊት የምንቆምበት ቀን ነው። ሁሉም ከመቃብር ተነስቶ የሠራውን ሥራ ዋጋ ሊቀበል በአሏህ ፊት ይቆማል። ይሄም ሥፍራ ያንን የሚያስታውስ ነው። ሰዎችም ከዚህ ተምረው ከኩራት፣ ከዘረኝነት፣ ከንቀት ርቀው፣ ለሀገር፣ ለአንድነት፣ ለሰላም መትጋት እንዳለባቸው የሚያስተምር ነው ይላሉ።

ለነብዩ ኢብራሂም በልጃቸው ፋንታ የቀረበው የበግ መስዋዕትነት ዛሬም ድረስ ለደሃዎች እየተከፋፈለ ይተገበራል። እርዱ ለሦስት ተከፍሎ፣ ለደሃዎች እና ለሌሎች ይከፋፈላል። በተለይም በዚህ ዘመን ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው በመጠለያ የሚኖሩ ወገኖች አሉ። የእኛ ልጆች እየሳቁ የአቅመ ደካማ ልጆች እያለቀሱ ሊያሳልፉ አይገባም። ዒዱ የሁሉም እንዲኾን ሃይማኖቱ በሚያዝዘው መሠረት መተግበር አለበት ነው የሚሉት ሼሁ። በአሏህ ፊት እኩል እንደኾናችሁ ሁሉ በእኩልነት ኑሩ። አንድነትን ባሕሪያችሁ እና ተግባራችሁ አድርጉ።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ በተለያዩ አጋጣሚዎች ችግሮች ሲገጥሟት ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጎን በመኾን ላሳየችው ድጋፍ እና ወዳጅነት እናመሰግናለን” አቶ አደም ፋራህ
Next articleበነብያቶች የተጎበኘችው ቅዱስ ከተማ – መካ