
እንጅባራ: ሰኔ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ)1 ሺህ 445ኛው የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓል በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እንጅባራ ከተማ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች ተከብሯል።
በበዓሉ የቢላል መስጂድ ኢማም ሼህ አብዱ ቡሽራ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ሼህ አብዱ በመልዕክታቸውም በዓሉ ነብዩ ኢብራሒም አንድየ ልጃቸውን ለመሥዋዕትነት በማቅረብ ለፈጣሪ ያላቸውን ፍጹም እምነት እና መታዘዝ የገለጡበት ነው ብለዋል።
ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩትን በመጠየቅ እና በመደጋገፍ ሊኾን እንደሚገባም ሼህ አብዱ አስገንዝበዋል። ወቅቱ ሰላም የታወከበት እና በርካታ ወገኖች ችግር ላይ የወደቁበት ነው ያሉት ሼህ አብዱ ሁሉም ወገን ለሰላም መትጋት እንዳለበትም ተናግረዋል።
የበዓሉ ታዳሚዎችም በዓሉን የተቸገሩትን በመጠየቅ እና ካላቸው በማካፈል በጋራ እንደሚያከብሩ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
