
ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በእስልምና አቆጣጠር የመጨረሻው ወር ላይ እንገኛለን። ወሩ ዙል-ሂጃ በመባል ይጠራል። ወሩ በገባ 10ኛው ቀን የዒድ አል አድሃ በዓል ይከበራል ይላሉ በወልዲያ ከተማ አሥተዳደር እስልምና ጉዳይ የዳዋ እና ትምህርት ዘርፍ ተጠሪ ኡስታዝ አብደላ መሐመድ።ዓረፋ የሚባለው ዋዜማው እንደኾነ የሚያስረዱት ኡስታዝ አብደላ መሐመድ ዋናው በዓል ዒድ አል አድሃ እንደሚባል ይናገራሉ።
👉በዓረፋ እለት ሙስሊሞች ምን ተግባር ያከውናሉ?
እንደእሳቸው ገለጻ ዓረፋ የቦታ ስም ነው። አደም እና ሀዋ የተዋወቁበት ቦታ እንደኾነም ታሪክ ያስረዳል። የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የዒድ አል አድሃ ዋዜማ በኾነው ዓረፋ ቀን ዓረፋ ተራራ ላይ ተገናኝተው በጋራ ዱዓ (ጸሎት) ያደርጋሉ። ሀጅ ያላደረጉ ሰዎች ደግሞ የዓረፋ ቀንን በፆም እናሳልፋለን ብለዋል ኡስታዝ አብደላ። ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) “ያችን ቀን የፆሙ የሁለት ዓመት (1 ዓመት ወደ ፊት አንድ ዓመት ወደኃላ) ወንጀል ይሰረዝላቸዋል” ብለዋል።
👉በዋናው ዒድ አል አድሃ በዓል ምዕመናን ምን ያደርጋሉ?
እንደ ኡስታዝ አብደላ ገለጻ በዒድ አል አድሃ በዓል ጠዋት ሙስሊሞች ገላቸውን ይታጠባሉ፤ አዲስ ልብሶችን ይለብሳሉ፤ ሽቶ ይቀባሉ፤ ፆማቸውን እንደኾኑ አሏሁ አክበር እያሉ ፈጣሪያቸውን እያወደሱ ወደ መስገጃ ቦታው ይሄዳሉ። መስገጃ ቦታ ላይ ተቀምጠው የተወሰነ ይጠብቃሉ። ከዚያም ላይ ፈጣሪያቸውን ያወድሳሉ። የተለያዩ ምክሮችን ከሃይማኖት አባቶች ያዳምጣሉ፤ ስግደቱ ሲጀመር ስግደቱን ያከናውናሉ ብለዋል።
ስግደቱ ከተጠናቀቀ በኃላ የእርድ ሥርዓቱ ይከናወናል። ይህ የበዓሉ ትልቅ ሥርዓት ነው። እርዱ ለፈጣሪ መስዋእት የሚቀርብበት ነው። የዒድ አል አድሃ በዓል የመሥዋትነት በዓል በመባልም ይጠራል። ይህ ታሪካዊ ዳራ አለው።
በዒድ አል አድሃ ቀን ነብዩ ኢብራሂም የመጀመሪያ ልጃቸውን እስማኤልን እንዲያርዱ የታዘዙበት ቀን ነው። ነብዩ ኢብራሂም በህልማቸው በኩል መልእክት ይደርሳቸዋል። እናም በህልማቸው ፈጣሪ ልጃቸው እስማኤልን እንዲሰውላቸው ይጠይቃቸዋል።
እስማኤልም የፈጣሪ ትዕዛዝ እንዲፈጸም ይስማማሉ። ከዚያም እስማኤል ለእርድ ይዘጋጃሉ። ፈጣሪም በእስማኤል ምትክ ትልቅ በግ አቀረበ። ይህ የኢብራሂም እና የልጃቸው እስማኤል ታላቅ እምነት ልክ የታየበት ነው። ነብዩ ኢብራሂም እና ልጃቸው ይህን ትልቅ ፈተና ያለፉበት እና እርድ የተፈጸመበት ቀን የዒድ አል አድሃ በዓል ተብሎ ይከበራል።
👉በበዓሉ አቅመ ደካሞች እንዴት ይደገፋሉ
በወልዲያ ከተማ አሥተዳደር እስልምና ጉዳይ የዳዋ እና ትምህርት ዘርፍ ተጠሪ ኡስታዝ አብደላ መሐመድ እናንተም ተመገቡ አቅመ ደካሞችንም መግቧቸው የሚል ሃይማኖታዊ አስተምህሮቱ ስለመኖሩ ይናገራሉ። በተለይም እርድ ከተከናወነ በኃላ ሲሶውን ለቤተሰብ፣ ሲሶውን ለአቅመ ደካሞች እንዲኹም ሲሶውን ለሚወዱት በስጦታ መልክ መስጠት እንደሚገባ ሃይማኖታዊ አስተምህሮቱ ያዛል ይላሉ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
