“የሀገር ችግር የሚፈታው በትምህርት በመኾኑ በሕጻናት ደረጃ ፆታን መሰረት አድርጎ የሚመጣ ማኅበራዊ ቀውስን መፍታት ያስፈልጋል” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

24

ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ ሕጻናት ቀን ” የሕጻናትን የትምህርት ተሳትፎ እና ጥራት የማሳደግ ጊዜው አሁን ነው” በሚል መሪ መልእክት በባሕር ዳር ከተማ ተከብሯል። የበዓሉ አዘጋጅ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ብርቱካን ሲሳይ እንዳሉት ሕጻናት በአካል እና በአዕምሮ ያልበሰሉ በመኾናቸው የኅብረተሰቡን እና የመንግሥትን ልዩ ድጋፍ ይሻሉ ብለዋል።

የሕጻናት መብቶች ከተጣሱ በዕድገታቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያስከትላል ያሉት ኅላፊዋ መንግሥትም ከዚህ አንጻር የሕጻናትን መብቶች ለማስከበር የሚያስችሉ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሕግ ድንጋጌዎችን አክብሮ እየተገበረ ይገኛል ነው ያሉት።

በሕገ መንግሥቱ ሕጻናት በሕይወት የመኖር፣ ከማንኛውም ጥቃት የመጠበቅ፣ ከጉልበት ብዝበዛ የመጠበቅ እንዲሁም ከአድልኦ ነጻ የመኾን መብቶቻቸው ተረጋግጧል ያሉት ወይዘሮ ብርቱካን እነዚህ መብቶች በተግባር እንዲከበሩ የተለያዩ የሕግ እና የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ ውጤት ተመዝግቧል ሲሉ ተናግረዋል።

ኅላፊዋ አያይዘውም መንግሥት ለሕጻናት መብት መከበር ከፍተኛ ትኩረት ቢሰጥም አሁንም በአማራ ክልል በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ወላጆቻቸውን በማጣት ውርስ መሬታቸውን ተነጥቀው ኑሯቸውን ጎዳና ላይ በማድረግ ለተለያዩ ጥቃቶች ሰለባ የኾኑ ሕጻናት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም ብለዋል። በዚህ ውስብስብ ችግር ውስጥ የሚገኙትን ሕጻናት ሕይዎት ለመታደግ የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ በመኾኑ ቢሮው በቅንጅት እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት።

“ሕጻናት የቤተሰብ፣ የሕብረተሰብ እና የመንግሥት ክብካቤ እና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰብዓዊ ቡቃያውዎች ናቸው” ያሉት ኅላፊዋ ለሕጻናት መብት መከበር ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን መረባረብ ይኖርብናል ብለዋል። የበዓሉ የክብር እንግዳ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር.) እንዳሉት በሕጻናት ትምህርት ላይ ከዚህ ቀደሙ በተሻለ መልኩ መዋእለ ነዋይን ልናፈስ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሕጻናትን በዕውቀት ቀርጾ የተሟላ ሰብዕና እንዲኖራቸው ለማድረግ አስፈላጊ የኾኑ አገልግሎቶችን አሟልቶ መብት እና ደኅንነታቸውን ለማስጠበቅ በተግባር በመሥራት ጥሩ ውጤት እየታየ ነው ብለዋል።

ሚኒስትሯ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሕጻናት የማንነት እና የሥነ ልቦና ችግር ሳይገጥማቸው በአምባ ውስጥ እንዲያድጉ እየሠራነውም ብለዋል። በአማራ ክልል በግጭት ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑ ሕጻናትን በውይይት እና ሰላምን በመሻት በጋራ ርብርብ ወደ ትምህርት ቤት ልንመልሳቸው ግድ ይለናል ብለዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር.) በበኩላቸው የሀገር ችግር የሚፈታው በትምህርት በመኾኑ በሕጻናት ደረጃ ፆታን መሰረት አድርጎ የሚመጣን ችግር እንዲሁም ግጭትን እና ማኅበራዊ ቀውስን መፍታት ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል።

የትምህርት ተቋማትን ማስፋፋት እና ግብዓት ማሟላትም ይገባል ባለዋል። የክልሉ መንግሥትም ኃላፊነቱን ለመወጣት ይተጋል ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ።
የአፍሪካ የሕጻናት ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ በአፍሪካ ደግሞ ለ34ኛ ጊዜ ተከብሯል።

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሕዝበ ሙስሊሙ የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓልን ሲያከብር በአብሮነት እና በመረዳዳት መንፈስ ሊኾን ይገባል” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ
Next articleየመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ማኅበረሰቡ የተቀላቀሉ ታጣቂዎች ሌሎችም የእነሱን ፈለግ እንዲከተሉ ጥሪ አቀረቡ።