የሌማት ትሩፋት ላይ የተሻለ ውጤት እየታየ መኾኑን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አስታወቀ።

30

ሰቆጣ: ሰኔ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር እንሰሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አዘጋጅነት የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም እና የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ መድረክ በሰቆጣ ከተማ ተካሂዷል። በንቅናቄ መድረኩም የብሔረሰብ አስተዳደሩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የእንሰሳት እና ዓሳ ሃብት ባለሙያዎች እና ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል።

በውይይቱም ወረዳዎች በሌማት ትሩፋት ላይ ያከናወኗቸው ጅምር የልማት ሥራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በሰቆጣ ከተማ አሰተዳደር በሌማት ትሩፋት ውጤታማ የኾኑ ወጣቶች ተጎብኝተዋል። የልምድ ልውውጥም ተደርጓል።

በዶሮ እርባታ የተሠማራው ወጣት ዮናስ ደባሽ በስሩ ለሰባት ወጣቶች የሥራ እድል የፈጠረ ሲኾን በራሡ ጥረት የዶሮ እርባታውን በማስፋፋት ጫጩቶችን ለተረካቢ ወጣቶች በማከፋፈል እና እንቁላልን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ውጤታማ ሥራ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ገልጿል። በቀጣይም የቦታ ድጋፍ ከተደረገለት ድርጅቱን በማስፋፋት ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል የመፍጠር እቅድ እንዳለው ገልጿል።

ሌላኛዋ በእንሰሳት እርባታ የተሠማሩት ወይዘሮ መሠረት ግርማ ከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸላቸው የማርቢያ ቦታ የላም ወተት ለገበያ በማብቃት የተሻለ ውጤት እያስመዘገቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በከተማ ሌማት ትሩፋት ከ10 በላይ ወጣቶች ተሰማርተው የተሻለ ውጤት እያስመዘገቡ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ የጉብኝቱ አስተባባሪ እና የሰቆጣ ከተማ እንሰሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ መቅደስ ሽዋረጋ በቀጣይም 20 አዳዲስ ወጣቶችን በሌማት ትሩፋት በማቀፍ ከእነዚህ ወጣቶች ተሞክሮ እንዲቀስሙ በማድረግ ለማሰማራት አቅደናል ብለዋል።

በሌማት ትሩፋት ሥራዎች ላይ የተሻለ ውጤት እያስመዘገብን ነው ያሉት ደግሞ የብሔረሰብ አስተዳደርሩ እንሰሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ ሲሳይ አያሌው ናቸው። በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ያለውን ጸጋ በአግባቡ በመጠቀም በተለይም በትምህርት ቤቶች የወተት ላሞችን በመጠቀም ህጻናት እንዲጎለብቱ በማድረግ በኩል የተጀመሩ ሥራዎች መስፋፋት እንደሚገባቸው ጠቅሰዋል።

ከቦታ ጋር ያሉ ጥያቄዎችንም ከሚመለከተው የመንግሥት ተቋም ጋር በመነጋገር እንደሚፈቱትም አቶ ሲሳይ አያሌው ገልጸዋል። በጉብኝቱ ማጠቃለያ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የብሔረሰብ አስተዳደሩ ዋና አስተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ ጸጋዎቻችንን ለይተን ከተጠቀምን በብሔረሰብ አስተዳደሩ ውስጥ ሥራአጥ ወጣት አይኖረንም ብለዋል።

በተከዜ ዓሳ፣ በእንሰሳት እርባታ፣ በንብ ማነብ ወዘተ ሥራዎች ተሠማርተው ውጤታማ የኾኑ ወጣቶች የዚህ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል። በቀጣይም አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ በርካታ ወጣቶች በሌማት ትሩፋት እንዲሰማሩ እንሰራለን ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዛሬ ደም በመለገስ የሰዎችን ሕይወት የሚታደጉ በጎ ፈቃደኞች የሚመሠገኑበት የዓለም የደም ልገሳ ቀን ነው።
Next articleየዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓል ሲከበር ከራስ በላይ ለሌሎች በማሰብ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ሊኾን እንደሚገባ የእስልምና ሃይማኖት አባቶች ገለጹ፡፡