“በአማራ ክልል ያለው የፋይናንስ አካታችነት ማዕቀፍ አሁን ካለበት 35 በመቶ ወደ 70 በመቶ ለማሳደግ እየተሠራ ነው” ብሔራዊ ባንክ

75

አዲስ አበባ: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ፕሮግራም እንደ ሀገር ተቀርጾ እየተሠራ ሲኾን ይህንን አካታችነት ለማሳደግ ፕሮግራሙን ክልላዊ ማዕቀፍ በመስጠት እየተሠራ ነው። የብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ሁለት መሠረት በማድረግ የተዘጋጀውን የአማራ ክልል የፋይናንስ አካታችነት ማዕቀፍ በክልሉ ለተደራጀው የፋይናንስ አካታችነት ምክር ቤት እና ግብረኀይል አባላት የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ ነው።

የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ፕሮጀክት አካታችነት ገለጻ እና ውይይት ላይ የብሔራዊ ባንክ የዘርፉ ኀላፊዎች፣ የአማራ ክልል የፋይናንስ እና ሌሎች የሚመለከታቸው የቢሮ ኀላፊዎች እንዲሁም የባንክ እና የኢንሹራንስ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል። የፋይናንስ አካታችነት ማለት የሴቶች እና የወንዶች የፋይናንስ ተጠቃሚነት ንፅፅር፣ የዲጂታል ገንዘብ ተጠቃሚዎች መጠን፣ የሸሪዓ ፍላጎት ፋይናንስ ተጠቃሚዎች፣ የወጣቶች እና መሰል የገንዘብ ተጠቃሚነት፣ የፋይናንስ መሪዎች ተዋጽኦ እና ሌሎች ላይ መሠረት ያደረገ ነው።

በብሔራዊ ባንክ የምክትል ገዥ አማካሪ ማርታ ሃብተማሪያም እንዳሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያው የፋይናንስ አካታችነት ፕሮግራም እንደ እ.ኤ.አ ከ2016 አስከ 2020 ተተግብሮ ተደራሽነቱ ከ22 በመቶ ወደ 45 በመቶ ደርሷል። አሁን ላይ ሁለተኛው ፕሮጀክት ይፋ ከተደረገ በኋላ በሚጠበቀው መጠን ማደግ ባለመቻሉ አዳዲስ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ክልላዊ ማእቀፍ እንዲይዙ ተደርገዋል ብለዋል።

ፕሮግራሙ ከአንደኛው ፕሮጀክት ተሞክሮ የተወሰደ ሲኾን አቅምን በመጨመር እና በማሳደግ የተለያዩ መተግበሪያዎችን መሠረት አድርጎ ይሠራል ብለዋል። በብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ አካታችነት ፕሮጀክት ቡድን መሪ አብርሀም ፈቃደ የአማራ ክልል የአካታችነት ምጣኔ 35 በመቶ ነው ብለዋል፡፡ ምጣኔው ከሌሎች ክልሎች የተሻለ ቢኾንም ከከተማ አሥተዳደሮች እና ከሀገር አቀፉ 45 በመቶ ዝቅ ያለ በመኾኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ካለው 70 በመቶ ለማድረስ የአካታችነት ፕሮጀክት ሁለት ዓላማው አድርጓል ብለዋል፡፡

የመጀመሪያው ስትራቴጂ ሲቀረጽ በኢትዮጵያ ከ22 ወደ 60 በመቶ ለማድረስ ታስቦ የተሠራ ቢኾንም ይህንን ማሳካት ባለመቻሉ እንደሀገር ይህንን ለማሳደግ ሲታሰብ በክልሎች ደረጃ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እንዲኾን እየተሠራ ነው ብለዋል በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የፋይናንስ አካታችነት ተጠቃሚዎች መጠን 46 በመቶ ብቻ መኾኑን ተናግረዋል።

የሞባይል ገንዘብ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እና ሌሎች አራት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ፕሮጀክት ሁለት ስትራቴጂ በመፍትሔነት ይዟቸዋል። የፋይናንስ አካታችነትን መፍጠር እንደሀገር ኢኮኖሚያዊ ፓለቲካዊ እና ማኅበራዊ መረጋጋትን ይፈጥራል ተብሏል።

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመንግሥት ተቋማት አገልግሎትን ወደ ኤሌክትሮኒክ ወይም ዲጀታል ሥርዓት ለማስገባት በትኩረት እየተሠራ መኾኑ ተገለጸ።
Next articleየክረምቱን መግባት ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ለመከላከል ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ተጠየቀ።