
ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በበጀት ዓመቱ ባለፉት 10 ወራት 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገልጸዋል። የ2016 በጀት ዓመት የመጨረሻ የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት ተካሂዷል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል የኢንዱስትሪ ዘርፉ በ10 ነጥብ 1 በመቶ እድገት መጨመሩን ገልጸው፣ የ7 ነጥብ 9 በመቶ ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገትን ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተከታታይ የተተገበረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለዘርፉ መነቃቃት ትልቅ ሚና መጫወቱንም ገልጸዋል። በዘርፉ አዳዲስ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ባለፉት 10 ወራት 129 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውንም ነው ሚኒስትሩ ያብራሩት።
በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ወደ ሥራ እንዲገቡ እና የማምረት አቅማቸው እንዲያድግ መደረጉንም አንስተዋል። በተጨማሪም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የፋብሪካ ምርቶችን ለመተካት በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
ለዚህም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኹነኛ ሚና እንዳለው በመግለፅ፣ በበጀት ዓመቱ ያለፉት 10 ወራት 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት መቻሉን ገልጸዋል። ይህ ውጤት በተሻለ መልኩ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማስቻልም በ2017 በጀት ዓመት በኢንዱስትሪ ዘርፉ የ12 ነጥብ 8 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ መታቀዱንም የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
0
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!