በአማራ ክልል መጠነኛ የገበያ መረጋጋት መኖሩን የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

28

ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በክልሉ ከባለፈው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ የገበያ መረጋጋት የሚታይበት የግብርና ምርት ዋጋ መኖሩን የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት አስታውቋል፡፡ በአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የሰብል እና ኢንዱስትሪ ምርት ግብይት ዳይሬክተር ልንገረው ሀበሻ ምርት በጅምላ ነጋዴዎች እና በሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት ለኅብረተሰቡ እየደረሰ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ከባለፈው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ የገበያ መረጋጋት የሚታይበት የግብርና ምርት ዋጋ መኖሩንም ገልጸዋል፡፡ ጅምላ ነጋዴዎች ምርት ካለበት አካባቢ እያሠባሠቡ ወደ ከተማ እያስገቡ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ለሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የገንዘብ ድጋፍ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ እያንዳንዱ ከተማ የራሱን አካባቢ የኑሮ ውድነት ለማቃለል ለሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ገንዘብ እያስመደበ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ገንዘቡን እየወሰዱ እየሠሩ መኾናቸውን አመላክተዋል፡፡ በአቅም የተሻሉ እና ምስጉን የሚባሉ ነጋዴዎችም ምርት ከሌላ ቦታ እያመጡ በየከተማው ከፍተኛ የኾነ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በመስኖ እየተመረቱ ያሉ ምርቶች ገበያውን እያረጋጉት መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ለአብነት በፎገራ አካባቢ እየተመረተ ያለው የጤፍ ምርት የጎንደርን ቀጣና የኑሮ ውድነት እያረጋጋው ነው ብለዋል፡፡

ገበያ ነጻ ዝውውር እንደሚፈልግ የተናገሩት ዳይሬክተሩ በየአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ ምርት እንደ ልብ እንዲዘዋወር እያደረገ አለመኾኑን ተናግረዋል፡፡ የጸጥታ ችግር በተለይም የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶች በወቅቱ እንዳይደርሱ እያደረገ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡ በመንገድ መዘጋጋት ምክንያት የሚበላሹ የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶች መኖራቸውን አስታውቀዋል፡፡

ይህ ደግሞ የኑሮ ውድነቱ በሚፈለገው መልኩ እንዳይረጋጋ ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡ ገበያ ሰላም እና ሕጋዊነቱን የተከተለ ነጻ ዝውውር እንደሚፈልግም ተናግረዋል፡፡ በክልሉ የተረጋጋ ሰላም ቢኖር የኑሮ ውድነቱ አሁን ካለው መጠነኛ መረጋጋት የበለጠ መረጋጋት ሊፈጠር እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡ ሰላም ሲኖር የገበያ ዝውውር ይኖራል፤ ምርትም በስፋት ይመረታል ነው ያሉት፡፡ የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት እና የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ሰላም እንዲኖር መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ29 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ የተገነባው የጥርሀሆ ድልድይ ለአገልግሎት ዝግጁ ኹኗል።
Next article“ብቁ እና ጤናማ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር የከተሞቻችንን ጽዳት መጠበቅ ልምድ ማድረግ ይኖርብናል” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)