
ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በምሥራቅ በለሳ ወረዳ የጥርሀሆ ወንዝ ድልድይ ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ ኾኗል። የድልድዩ መገንባት ከፍተኛ የኾነ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። ከዚህ በፊት በኅብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ እንግልት ያደርስ የነበረው የጥርሀሆ ወንዝ ድልድይ በክልሉ መንግሥት በጀት 29 ሚሊዮን 788 ሺህ 589 ብር በኾነ ወጪ ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ በመኾኑ ለማኅበረሰቡ ጥያቄ ምላሽ አስገኝቷል።
የወረዳው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት የጥርሀሆ ወንዝ በክረምት ወቅት ከአቅም በላይ ስለሚሞላ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸው ላይ ተጽእኖ ሲያሳድር መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን በወንዙ ላይ የተገነባው ድልድይ ክረምት ሲመጣ ወንዝ ለመሻገር ያለባቸውን ስጋት መቅረፉንም ተናግረዋል፡፡
የምሥራቅ በለሳ ወረዳ ሕዝብ ላለፉት በርካታ ዓመታት በመንገድ መሠረተ ልማት እጦት ሲቸገር መቆየቱን የተናገሩት ደግሞ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን መንገድ መምሪያ ኀላፊ አስንቃ ክብካብ ናቸው። ኀላፊዋ በክልሉ መንግሥት የተገነባው የጥርሀሆ ወንዝ ድልድይ የአካባቢው ነዋሪዎችን የዘመናት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነውም ብለዋል።
የድልድዩ መገንባት የአካባቢውን ነዋሪዎች ከስጋት ነፃ ያደረገ እንደኾነ ያብራሩት ወይዘሮ አስንቃ ክብካብ ድልድዩ በርካታ ቀበሌዎችን ተጠቃሚ ከማድረጉ በተጨማሪ ለዞዝ አምባ ጊዮርጊስ የቱሪዝም ፍሰት ፋይዳው የጎላ ነውም ብለዋል። ከክልሉ ገጠር መንገድ ቢሮ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ እንዳገኘነው መረጃ የጥርሀሆ ወንዝ ድልድይ ጎሀላ ከተማን ከዞዝ አምባ ቀበሌ የሚያገናኝ ሲኾን በዓባይ ግድብ ተቋራጭ ኅብረት ሥራ ማኅበር አማካኝነት ሲገነባ ሽሎ አማካሪ የባለሙያዎች ማኅበር ደግሞ የማማከር ሥራውን ሠርቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!