
ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ከሰሊጥ፣ ከማሾ፣ ከአኩሪ አተር፣ ከጥጥ እና ሌሎች ሰብሎች በተጨማሪ በተከዜ ወንዝ ዳርቻ ፍራፍሬ በስፋት ይመረታል፡፡ የአካባቢው ተወላጅ ባለሃብቶች የተከዜን ወንዝ በመጠቀም አትክልት እና ፍራፍሬ በስፋት ማምረት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
እያመረቱት ያለው የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት ታዲያ የገበያ ትሥሥር ባለመኖሩ ለኪሳራ እየተዳረጉ መኾናቸውን ነው የገለጹት፡፡ የገበያ ትሥሥር ቢኖር ኖሮ በኑሮ ውድነት ለሚቸገረው ማኅበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ ማድረስ ይቻል እንደነበርም አንስተዋል፡፡ በሁመራ ዙሩያ የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት እያለሙ የሚገኙት ፈረደ ነጋ የሽንኩርት ልማታቸው አበረታች እና ጥሩ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
አልሚው ባለሃብት አቶ ፈረደ የተለቀመ 800 ኩንታል ሽንኩርት እንዳላቸው ነው የተናገሩት፡፡ በማሳው ያልተለቀመ ሽንኩርት እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡ ልማቱ በስፋት ምርት ቢሰጥም የገበያ ትሥሥር ባለመኖሩ በመካዘን ለመከዘን ተገድደናል ነው ያሉት፡፡ ሌሎች አልሚ የመስኖ ባለሃብቶች ምርታቸውን በመጋዘን ለማስቀመጥ መገደዳቸውንም አመላክተዋል፡፡
በቀጣይ ጊዜያት በሞራልም ኾነ በምጣኔ ሃብት ታግዘን እንድንሠራ ከተፈለገ ከውጭ የሚገባው ምርት ቀንሶ ለእኛ ትኩረት ሊሰጠን ይገባል ብለዋል፡፡ የሀገር ውስጥ ምርት ሕዝቡን በማይጎዳ ተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚደርስ እና አልሚዎችንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ነው የተናገሩት፡፡
በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግርም ሽንኩርት ወደ ገበያ እንዳይቀርብ እንቅፋት ሳይኾን እንዳልቀረ ነው የገለጹት፡፡
ለሽንኩርት ልማት 9 ሚሊዮን ብር ማውጣታቸውን የተናገሩት አልሚው የገበያ ትሥሥር ሊፈጠርልን ባለመቻሉ ለኪሳራ እየተዳረግን ነው ብለዋል፡፡ ካመረትነው ምርት አንድም ኪሎ ሽንኩርት አልሸጥንም ነው ያሉት፡፡ ሽንኩርት በጊዜው ለገበያ ካልቀረበ እንደሚበላሽም ተናግረዋል፡፡ ምርቱን ለማምረት ከፍተኛ ጥረት አድርገው እንደነበርም አንስተዋል፡፡
የገበያ ትሥሥር ከልተፈጠረ ትርፍ ማትረፍ ሳይኾን ወረታችን እናጣለን ነው ያሉት፡፡ መንግሥት የገበያ ትሥሥር እንዲፈጥርላቸው እና ወደ ሕዝብ እንዲያቀርቡ እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡ ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው 6 ሺህ 749 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ 5 ሺህ 522 ሺህ ሄክታር መሬት ለምቷል፡፡
በመስኖ ከለማው ማሳ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት ተችሏል፡፡ በሽንኩርት ከለማው 2 ሺህ 280 ሄክታር መሬት 715 ሺህ ኩንታል ምርት ተገኝቷል፡፡ በአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የሰብል እና ኢንዱስትሪ ምርት ግብይት ዳይሬክተር ልንገረው ሀበሻ ከሚያዚያ ወር ጀምሮ እስከ ሰኔ መጀመሪያ ድረስ ያለው ወቅት ሁሉም አምርቶ ለገበያ የሚያቀርብበት በመኾኑ ችግር እንደሚፈጠር ነው የተናገሩት፡፡ ይህ ወቅት በተደጋጋሚ የገበያ መውረድ ችግር እንደሚከሰትበትም ገልጸዋል፡፡
በዚህ ወቅት በስፋት የሚያምርቱ አምራቾች መክሰር እንደሌለባቸውም ተናግረዋል፡፡ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ላይ ሽንኩርት በስፋት መመረቱን የሚያሳይ መረጃ አለመኖሩን ነው የገለጹት፡፡ የተፈጠረው የመረጃ ክፍተትም ባለሃብቶች ገበያ አጣን እንዲሉ ማድረጉን ነው ያነሱት፡፡ ሽንኩርት በየከተማው እንደሚፈለግም ተናግረዋል፡፡
በዚህ ወቅት የሀገር ውስጥ ምርት ብቻ ሳይኾን የሱዳንም ምርት በስፋት ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ መኾኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ገበያውን ለማረጋጋት የሽንኩርት ምርት በስፋት እንዲገባ እንደሚፈለግም ገልጸዋል፡፡ ሽንኩርት በአንድ ወቅት በጣም ሲወደድ ሁልጊዜም ዋጋው እንደዛ ኾኖ ይቀጥላል በሚል እሳቤ ሁሉም በበጋ መስኖ በስፋት እንደሚያመርትም ተናግረዋል፡፡
ከፍተኛ ዋጋ እናገኛለን በሚል የማምረቻ ወጪን እንደሚጨምሩም ገልጸዋል፡፡ ገበያው እንዲረጋጋ መንግሥትም ሕዝቡም ሽንኩርት በስፋት እንዲኖር እንደሚፈልግም አመላክተዋል፡፡ ባለሃብቶች እንደ ሁልጊዜው በውድ እንዲሸጥላቸው መፈለግ እና ወቅቱ ደግሞ በርካታ ሽንኩርት ተመርቶ ወደ ገበያ የሚገባበት መኾኑ የጥቅም አለመጣጣም እንዲመጣ ማድረጉን ነው የተናገሩት፡፡
ሽንኩርትን እንደሌሎች ምርቶች በመጋዘን ማቆየት አለመቻልም ሌላው ችግር መኾኑን ነው የገለጹት፡፡ ሽንኩርትን የተሻለ መጋዘን ሠርቶ እስከ ሦስት ወር ድረስ ማቆየት እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡ አልሚዎች የድሕረ ምርቱን አያያዝ ማስተካከል ቢችሉ የተሻለ ገበያ እንደሚያገኙም አመላክተዋል፡፡ ባለሃብቶች ምርቱን ከመሠብሠባቸው አስቀድሞ ወደ ምርት ሲገቡ የገበያ ትሥሥር የሚያገኙበትን መንገድ ማማከር እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡
ከማምረታቸው በፊት ካማከሩ አንድ ሰብል ብቻ ሳይኾን የተለያዩ ሰብሎችን በማምረት ራሳቸውንም ማኅበረሰቡንም ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡ሳያማክሩ ወደ ምርት መግባት አምራቾችን እንሚጎዳም አንስተዋል፡፡ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የተመረተው ምርት ወደ ገበያ የሚገባበትን ሁኔታ እየተነጋገርን ነው፤ የቀረው ምርት የገበያ ትስስር እንዲፈጠርለት ይመቻቻል ብለዋል፡፡ የጅምላ ነጋዴዎች እንዲያመጡ እና ለኅብረተሰቡ እንዲያደርሱ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ቴክኖሎጅን በመጠቀም ሽንኩርት እና ሌሎች ምርቶች ረጅም ጊዜ የሚቆዩበትን አማራጭ መጠቀም ይገባል ብለዋል፡፡ የአካባቢው ባለሃብቶች በሌሎች ምርቶችም ተጠቃሚ እንዲኾኑ እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!