
ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እያደረጉ ስለሚገኙ የጃፓን ባለሃብቶች ዙሪያ ከኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ ጋር መክረዋል። በምክክራቸውም በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ እንዳሉት ተጨማሪ የጃፓን ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ነፃ የንግድ ቀጣና ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጠንካራ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ከአምባሳደሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ እና ጃፓን ካላቸው ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ጠንካራ ወዳጅነት አንፃር የጃፓን ኢንቨስተሮች በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ያላቸው ተሳትፎ እና ድርሻ እንደሚጠበቀው አለመኾኑን ገልጸውላቸዋል፡፡
ተሳትፏቸውን ለማሳደግም በትብብር መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት። ለዚህም ኮርፖሬሽኑ ከምንግዜውም በላቀ መልኩ ዝግጁ መኾኑን አረጋግጠዋል። በኢንዱስትሪ ፓርኮች እያመረቱ የሚገኙ ዓለም ዓቀፍ እና ሀገር በቀል ኩባንያዎች አሁን ላይ ካላቸው ገበያ በተጨማሪ የጃፓንን ሰፊ የገበያ አቅም መጠቀም በሚችሉባቸው መንገዶች ላይ ምክክር ተደርጓል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው በቅርቡ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ፓስፖርትን ጨምሮ ዓለም ዓቀፍ የደኅንነት መስፈርቶችን የሚያሟሉ ምስጢራዊ የህትመት ውጤቶችን የሚያመርት ቶፓን ግራቪቲ የተሰኘ ግዙፍ የጃፓን ኩባንያ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ መቀመጡ ይታወሳል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!