የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታየ አፅቀሥላሴ ከሳዑዲ አረቢያ የንግድ ምክር ቤት ሰብሳቢ ጋር ተወያዩ።

21

ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታየ አፅቀሥላሴ ከሳዑዲ አረቢያ የንግድ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሀሰን ሙጂብ ኦል ህዋይዚ ጋር ተወያይተዋል። ሚኒስትሩ የሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ እያደረጉት ያለውን የኢንቨስትመንት እና ንግድ ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ሀገራት ባለሃብቶችን ለመሳብ ሰፊ የማሻሻያ ሥራዎችን በመሥራት ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢያዊ ሁኔታን እየፈጠረች እንደምትገኝ ሚኒስትሩ ገልፀዋል። በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዘርፍ በመሰማራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

የሳዑዲ አረቢያ የንግድ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሀሰን ሙጂብ በበኩላቸው፣ የሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት እና ንግድ በተለይም በግብርና ምርቶች ማቀነባበር እና በማምረቻ ዘርፎች ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ገልፀዋል። በዚህም የተመረጡ የሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶች በመጪው ነሀሴ ወር በኢትዮጵያ የቢዝነስ ጉብኝት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

አምባሳደር ታየ አፅቀሥላሴ የሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት በማሳየት በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ መወሰናቸው በሀገራችን በኩል የሚበረታታ መሆኑን ገልፀው፣ ኢትዮጵያ ተቀብላ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗንም አብራርተውላቸዋል። አያይዘውም የባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ እና የህዝብ-ለህዝብ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር አጋዥ እንደሆነ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ምቹ የመኖሪያ እና አረንጓዴ አካባቢ የሚያካትተው አዲሱን የመኖሪያ ህንፃ ግንባታ በመጪው መስከረም ወር ለማጠናቀቅ ዛሬ አስጀምረናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)የቻይና ኮሚኒኬሽን እና ኮንስትራክሽን ካምፓኒ (ሲሲሲሲ) ሊቀመንበር ዋንግ ቶንግዙን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለዋል።