የክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኮሮናን ለመከላከል ምን ያህል ዝግጁ ነው?

310

ሕር ዳር፡ መጋቢት 04/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኮሮና ቫይረስ ተከስቶባቸው ከነበሩ ሀገራት ወደ አማራ ክልል የገቡ 24 ግለሰቦች ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የኢንስቲትዩቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ባለሙያ አቶ አሞኘ በላይ ለአብመድ እንዳስታወቁት በሽታው ተከስቶ ጉዳት ከማድረሱ በፊት መከላከል የሚቻልባቸው ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ እየተደረገ ነው፡፡ ለቫይረሱ ሥርጭት አጋላጭ አካባቢዎችን ለይቶ የመከታተል፣ የቅኝትና የአሰሳ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በሚገኙ አራት የአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ በቱሪስት መዳረሻዎችና በትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች የሙቀት ልኬታ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተከናወኑ መሆኑን ባለሙያው አሳውቀዋል፡፡

በባሕር ዳር አውሮፕላን ማረፊያ ከሦስት ቀናት በፊት ጀምሮ በህክምና ባለሙያዎች የሙቀት ልኬታ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነም አቶ አሞኘ ተናግረዋል፡፡ የሙቀት ልኬታውን በጎንደር፣ በላል ይበላና በኮምቦልቻ አውሮፕላን ማረፊያዎች ለማከናወንም ቁሳቁስ እየተጓጓዘ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይ ቀናት (የኢንፍራርድ ቴርሞ ሜትር) ልየታው ይጀመራል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት ቫይረሱ ተከስቶባቸው ከነበሩ ሀገራት ወደ ክልሉ የገቡ 24 ግለሰቦች ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነም ተመላክቷል፡፡ ግለሰቦቹ ክትትል የሚደረግላቸው ስጋት ከነበረባቸው ሀገራት በመምጣታቸው ብቻ እንጂ ምልክቱ ታይቶባቸው አለመሆኑን ባለሙያው ገልጸዋል፡፡

በኮምቦልቻ አንድ የውጭ ሀገር ዜግነት ያለው ግለሰብ “ምልክቱ ታይቶበታል” ተብሎ የነበር ቢሆንም በምርመራ ነፃ መሆኑ መረጋገጡን አቶ አሞኘ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እንደ መተማ ባሉ የክልሉ ጠረፋማ አካባቢዎች፣ የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲሁም ውጭ ሀገራት ግለሰቦችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በሚገኙባቸው 44 ፕሮጀክቶች የቅኝትና የአሰሳ ተግባር እየተሠራ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡

በእነዚህ ቦታዎ የሙቀት ልየታ፣ የተያዙ ቢገኙም ህክምና ሊሰጡ ለሚችሉ የህክምና ባለሙያዎች ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱና ወደ አካባቢያቸው መመለሳቸውም ተረጋግጧል፡፡ የለይቶ ክትትል ማድረጊያ ስፍራዎችን የማመቻቸት ተግባርም እየተወጣ እንደሚገኝ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ አሳውቋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

Previous articleኬንያ ውስጥ ኮሮና ቫይረስ መግባቱ ተረጋገጠ።
Next articleፋሲል ከነማ በፕሪሚዬር ሊጉ መሪነቱን አስጠብቋል፡፡