“ቅዱስ ቁርአን በአላህ ፈቃድ ቃሉን በጂብሪል አማካኝነት ለነብዩ ሙሐመድ የወረደ የአላህ ቃል ነው” ኡስታዝ ሙሀመድ ሀሰን

31

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቅዱስ ቁርአን በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ቅዱስ መጽሐፍ ተብሎ ይጠራል፡፡ በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ቅዱስ መጽሐፉ በአላህ ፈቃድ ቃሉን በጂብሪል አማካኝነት ለነብዩ ሙሐመድ የወረደ የአላህ ቃል ነው ተብሎም ይታመናል።
ቅዱስ ቁርአን ለመጀመርያ ጊዜ በአረብኛ ቋንቋ ነበር የተጻፈው። የሃይማኖቱ ተከታዮች በልጅነት እድሜያቸው ቅዱስ ቁርአንን ለመቅራት ወደ “አሸር” በማምራት ይማራሉ።

በደብረ ብርሃን ከተማ መስጅደል ፈትህ የቁርአን መምህር ኡስታዝ ሙሀመድ ሀሰን ልጆች በ”አሽር” ቤት ቆይታቸው በሃይማኖቱ የሚታዘዙ ትእዛዛትን እንዲያከብሩ እና ለዲናቸው የተገዙ እንዲኾኑ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡ መምህሩ የተስተካከለ ስብእና እንዲኖራቸው ተደርገው እንደሚማሩም ነግረውናል።
በ”አሽር” ቤት ቁርአን ሲቀራ ሁሉም የራሳቸው የኾነ አቀባበል ስላላቸው እንደ አቀባበላቸው በልዩነት ቁርአንን እንደሚቀሩ ነው ያስገነዘቡት።

ቁርአን ሲቀሩ በሥነ ምግባር የታነጹ ኾነው ለዱንያም ለቀጣዩም ዘላለማዊ መንገድ የሚጠቅማቸውን ሥራ እንዲሠሩ እና በተስተካከለ የሕይወት መንገድ እንዲጓዙ እንደሚያስችላቸው ነው መምህሩ የገለጹት፡፡ ቁርአን መቅራት በ”አሽር” ቤት ቆይታቸው ከሚወስዷቸው ትምህርቶች ዋነኛው እንደኾነም መምህሩ ኡስታዝ ሙሀመድ አስገንዝበዋል።

እስልምና የራሱ የኾኑ ሥርአቶች ያሉት ሲኾን እነዚህን ተግባራዊ እንዲያደርጉ እና ለቤተሰብ የሚታዘዙ፣ ለሃይማኖታቸው የሚገዙ እንዲሁም ለሀገር የሚታመኑ እንዲኾኑ መሠረቱ የልጅነት ጊዜ የ”አሽር” ቤት ቆይታቸው እንደኾነም ኡስታዝ ሙሀመድ ገልጸዋል። የተማሯቸውን ትምህርቶች እንዲተገብሩ እና ብቁ ዜጋ እንዲኾኑ ማድረግ ደግሞ የወላጆች ኀላፊነት በመኾኑ የሌሎችን እምነት እንዲያከብሩ እና ተሳስቦ የመኖር ባሕል እንዲያዳብሩ መሠራት እንዳለበትም ኡስታዝ ሙሀመድ ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡- ስንታየሁ ኃይሉ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article1ሺህ 445ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል በደብረ ብርሃን ከተማ እየተከበረ ነው።
Next article1ሺህ 445ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው።