
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አወቀ አስፈሬ በወቅታዊ ጉዳዮች እና ቢሮው እየተገበራቸው በሚገኙ ሥራዎች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸው የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። በክልሉ በተለያየ ጊዜ የተጀመሩ 214 ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እየተደረጉ መኾናቸውን አስታውቀዋል። ፕሮጀክቶቹ 26 ሺህ 353 ሄክታር መሬት ማልማት የሚችሉ ናቸው ብለዋል። ከ44 ሺህ 126 በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም አመላክተዋል።
የክልሉ መንግሥት ለመስኖ ልማት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ያሉት ምክትል ኀላፊው ለፕሮጀክቱ ከ9 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ውል የተያዘባቸው መኾናቸውን ተናግረዋል። በዓመቱ 134 ፕሮጄክቶችን ለመሥራት አቅደው 95 ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል። 30 ፕሮጄክቶች መጠናቀቃቸውንም ገልጸዋል። የፕሮጀክት አፈፃፀማቸው ከባለፈው ዓመት የተሻለ መኾኑንም አንስተዋል። መጠናቀቅ የሚገባቸው ፕሮጄክቶች በጸጥታ ችግር ምክንያት መስተጓጎላቸውን አመላክተዋል።
በጸጥታው ችግር ምክንያት በርካታ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ አለመግባታቸውን አስታውቀዋል። በአግባቡ ያልተፈጸሙ 18 ፕሮጀክቶችን ውል ማቋረጣቸውንም ገልጸዋል። 119 ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ደረጃ አለመሄዳቸውንም አመላክተዋል። በቢሮው ከ14 ሺህ በላይ የሞተር ፓምፖች መሰራጨታቸውን አስታውቀዋል። የሞተር ፓምፖቹ ለአርሶ አደሮች የማዳረስ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በአንዳንድ ዞኖች ላይ በገጠመው የጸጥታ ችግር ምክንያት ለአርሶ አደሮች ለማድረስ እንቅፋት መፈጠሩን አንስተዋል። ቢሮው ፕሮጀክቶቹ በዘላቂነት የኅብረተሰብን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
የመስኖ ውኃ ማኅበራትን በማቋቋም ዘላቂ ተጠቃሚነት እንዲኖር እንደሚሠሩ የገለጹት አቶ አወቀ፤ በዓመቱ 231 ማኅበራትን ለማቋቋም ታቅዶ 75 ማኅበራትን አቋቁመናል ነው ያሉት። አፈፃፀሙ እንዲያንስ ያደረገው በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ነው ብለዋል። በተለያየ ጊዜ የተሠሩ ፕሮጀክቶች ጥገና መሠራቱንም ገልጸዋል።
በዓመቱ 29 የመስኖ ፕሮጀክቶችን ጥናት እና ዲዛይን ሠርቶ ለማጠናቀቅ ታቅዶ 6 መስኖዎችን ማጠናቀቅ ተችሏል ነው ያሉት። የጸጥታ ችግር በሌለባቸው አካባቢዎች በትኩረት ለመሥራት በመግባባት በቀሪ ጊዜያት የርብርብ ማዕከል ይኾናሉ ብለዋል። የመኪናዎች እንቅስቃሴ መገደብ የሲሚንቶ ችግር እንዲፈጠር አድርጓል ነው ያሉት። የተቋራጮች የአቅም ውስንነትም ሌላኛው ችግር መኾኑን ነው ያነሱት። የተሟላ የሰው ኀይል አለመኖሩም ሌላው ችግር ነው ተብሏል። የሰው ኀይል ችግሩን ለመፍታት ያለውን የሰው ኀይል በሚገባ የመጠቀም ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
የፕሮጀክቶች ተቋራጮቹ ሲንቀሳቀሱ በየቦታው በተደራጀ ሌባ እና ጽንፈኛ ቡድን ከአቅም በላይ የኮነ ገንዘብ እየተጠየቁ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። በተቋራጮች ላይ የሚደርሰው እንግልት ፕሮጀክቶችን በሚፈለገው ደረጃ ለመፈጸም እንዳላስቻለ ነው የገለጹት። በቀሪ ጊዜያት የተሻሉ ሥራዎችን ለመሥራት አርሶ አደሮች እና ሌሎች አካላት ከጎናቸው ኾነው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!