“ከ210 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው” የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ

16

ደብረ ብርሃን: መጋቢት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሰላም እጦቱ የትምህርት ዘርፉን በከፍተኛ ደረጃ እንደጎዳው የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታውቋል። መምሪያው ትኩረቱን በትምህርት ዘርፉ እንቅስቃሴ ላይ ያደረገ መግለጫ ሰጥቷል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ታደሰ ሸዋፈራው በሰጡት መግለጫ በዞኑ ያጋጠመው የሰላም እጦት የትምህርት ዘርፉን ክፉኛ ጎድቶታል ነው ያሉት።

ምክትል መምሪያ ኀላፊው እንዳሉት በቅድመ መደበኛ፣ በአንደኛ ደረጃ እና በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች “ከ210 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው” ብለዋል። እንደ ምክትል ኀላፊው ገለጻ በበጀት ዓመቱ ይመዘገባሉ ተብለው በእቅድ ከተያዙ 322 ሺህ ተማሪዎች መካከል የተመዘገቡት 224 ሺህ ተማሪዎች ብቻ ናቸው። ከነዚህ መካከል ደግሞ እየተማሩ ያሉት 124 ሺህ ተማሪዎች ብቻ ናቸው ብለዋል፡፡

ከ1 ሺህ 21 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል 680 ገደማ የሚኾኑት ብቻ ተከፍተው የመማር ማስተማር ሥራውን እያስቀጠሉ መኾኑን ተናግረዋል። በዞኑ ከሚገኙት 23 ወረዳዎች መካከል 22 ወረዳዎች ተማሪዎችን ተቀብለው እያስተማሩ ሲኾን ጽንፈኞቹ በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች የመማር ማስተማር ተግባሩ እክል የገጠመው መኾኑን አቶ ታደሰ ገልጸዋል።

ይህም የፀጥታ ችግሩ በመማር ማስተማር ሥራው ላይ ተጽእኖ ለማሳደሩ ማሳያ ነው ብለዋል። ዞኑ በችግር ውስጥ ኾኖም የትምህርት ተቋማትን በአዲስ እየገነባ መኾኑን ጠቅሰዋል። በአንዳንድ ወረዳዎች ላይ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሳደግ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አመላክተዋል።

በክልሉ ትምህርት ቢሮ፣ በፌዴራል ትምህርት ሚኒስቴር፣ ከዓለም ባንክ እንዲሁም መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በልዩ ልዩ ወረዳዎች የሚሠሩት እነዚህ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል። የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት በማሟላት ረገድ ከ82 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው መቀመጫ ወንበሮች በየትምህርት ቤቶች እንዲቀርቡ ተደርጓል ነው የተባለው።

ለአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የተዘጋጁ መጻሕፍት ታትመው እየተሰራጩ ሲኾን ከፀጥታ ችግሩ ጋር በተያያዘ መጻሕፍት ያልደረሳቸው ትምህርት ቤቶች መኖራቸውንም አቶ ታደሰ ገልጸዋል። የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችን በኦንላይን የመመዝገብ ሥራው እየተከናወነ ሲኾን እስካሁን ከሰባት ትምህርት ቤቶች ውጪ 91 በመቶ ተማሪዎች ተመዝግበዋል። የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ምዝገባም ነገ እንደሚጠናቀቅ ምክትል ኀላፊው ገልጸዋል፡፡
የተዘጉ የትምህርት ተቋማት እንዲከፈቱ እየተሠራ ነው ያሉት ምክትል ኀላፊው የፖለቲካ መሪዎች ብርቱ ተልዕኮ ወስደው ችግሩ እንዲቃለል እየሠሩ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከምጥ በላይ የሰላም እጦት የፈተናቸው እናት!
Next articleበአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከ84 በላይ ተንጠልጣይ ድልድዮች እንደሚገነቡ ተገለጸ።