የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ የመጀመሪያውን ወሰነ ትምህርት ማጠቃለያ ፈተና እየሰጠ መኾኑን አስታወቀ።

14

ባሕር ዳር: ጥር 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ኃይለማርያም እሸቴ በሰጡት መግለጫ በዞኑ የ2016 የትምህርት ዘመን የአንደኛው ወሰነ ትምህርት ፈተና እየተሰጠ መኾኑን ገልጸዋል።

እንደ ኀላፊው ገለጻ 74 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 16 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ፈተናውን እየሰጡ ነው። 2 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በቅርብ ቀናት ውስጥ ፈተናውን እንደሚሰጡ ነው ኀላፊው የተናገሩት።

ጢስ ዓባይ፣ መሸንቲ እና ዘንዘልማ ሳተላይት ከተሞች የሚገኙ 16 አንደኛ ደረጃ እና 3 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም በጸጥታ ችግር ምክንያት ስላላስተማሩ ፈተና እየሰጡ አለመኾናቸውን ነው አቶ ኃይለማርያም የገለጹት።

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ፈተናውን በራሳቸው ያዘጋጁ ሲኾን ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ፈተናው ተዘጋጅቶ መሰራጨቱን ገልጸዋል።

ትምህርት ሳይሰጥባቸው በቆዩ ትምህርት ቤቶች የክልሉ መንግሥት በሚሰጠው አቅጣጫ እና በሚወጣው ፕሮግራም መሠረት ትምህርቱ እና ፈተናው እንደሚሰጥ ነው አቶ ኃይለማርያም የገለጹት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምክር ቤቱ 14ኛ መደበኛ ጉባዔውን ነገ ከጠዋቱ 2፡00 ጀምሮ ያካሂዳል፡፡
Next articleማውሪሲዮ ፖቸቲኖ ከቼልሲ የመሰናበት አደጋ ተጋርጦባቸዋል።