በመስኖ ልማት 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየሠራ መኾኑን የሊቦ ከምከም ወረዳ አስታወቀ።

50

ባሕር ዳር: ጥር 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በመስኖ ልማት 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየሠራ መኾኑን በደቡብ ጎንደር ዞን የሊቦ ከምከም ወረዳ አስታውቋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን እና የሊቦከምከም ወረዳ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የመከላካያ የጦር መኮንኖች በታችኛው ርብ የመስኖ ፕሮጄክት የሚገኘውን የመስኖ ልማት ተመልክተዋል።

በአካባቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮች ከዓመታት ጥያቄዎች በኋላ የርብ መስኖ ፕሮጄክት ማልማት መጀመሩ ደስታ እንደፈጠረላቸውም ገልጸዋል። የተጀመረው የመስኖ ፕሮጄክት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል። አሁን ላይ አዲስ ሕይወት እና አዲስ ልማት እያዩ መሆናቸውንም አመላክተዋል።

የሽና ጽዮን ቀበሌ ነዋሪው ደጉ አምባው በርብ የመስኖ ፕሮጄክቶች የስንዴ ምርት እያመረቱ መኾናቸውን ገልጸዋል። የስንዴ ምርቱ የተሻለ መኾኑንም ተናግረዋል። የርብ ግድብ በተደጋጋሚ እንዲያለሙ እያደረጋቸው መኾኑንም ገልጸዋል።

የቡራ ቀበሌ አርሶ ደርብ አሰፋ ርብ የሰጠን ጥቅም ብዙ ነው ብለዋል። ከአሁን ቀደም እንኳን ለመስኖ ለከብት መጠጥ ውኃ እንቸገር ነበር ነው ያሉት። ርብ ከመጣ ጊዜ ጀምሮ በርከታ ጠቀሜታ እያገኙ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። በመስኖ ፕሮጀክቱ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ሽንኩት እና ሌሎች ምርቶችን እንደሚያመርቱም ገልፀዋል።

የሊቦከምከም ወረዳ መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አዝመራው ብርሃን በወረዳው የታችኛው ርብ መስኖ ፕሮጄክት ከ800 ሄክታር በላይ ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። አሁን ላይ ከ700 ሄክታር በላይ መሬት እየለማ ነው ብለዋል። ፕሮጄክቱ በሙሉ አቅሙ ሲያለማ ከ3 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ገልፀዋል።

የሊቦ ከምከም ወረዳ ግብርና ጽሐፈት ቤት ኃላፊ ነጋ ወንዱ በወረዳው በሚገኙ 31 ቀበሌዎች 18 ፕሮጄክቶች በመስኖ ተጠቃሚዎች ናቸው ብለዋል። በመስኖ ፕሮጄክቱ 8 ቀበሌዎች ተጠቃሚዎች መኾናቸውን ነው ያነሱት። የርብ የመስኖ ፕሮጄክቶች የመጀመሪያ ምዕራፍ ወደ ሥራ መግባት አርሶ አደሮች በተደጋጋሚ እንዲያመርቱ ማድረጉን ነው የገለፁት።

በወረዳው 13 ሺህ 924 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት እየተሠራ መሆኑንም ገልፀዋል አቶ ነጋ። በመስኖ ከሚሸፈነው መሬት 70 በመቶው የርብ መስኖ ፕሮጄክቶች መኾኑንም ተናግረዋል። በመስኖ ይለማል ተብሎ ከታቀደው 11ሺህ 986 ሄክታር መሬት ማልማታቸውንም ገልፀዋል።
በመስኖ ልማት 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱንም አመላክተዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ የሊቦከምከም ነዋሪዎች የአካቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ በልማት ሥራ ላይ መሰማራታቸውንም ገልጸዋል። የፎገራ እና የሊቦ ከምከም አካባቢዎች ለሀገር የሚተርፍ አቅም ያላቸው መኾናቸውንም ተናግረዋል። የርብ መስኖ ፕሮጄክት ምርትና ምርታማነትን ለመጨረመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።

ርብን በሚገባው ልክ መጠቀም መጀመሩንም ገልጸዋል። አርሶ አደሮች የጀመሩትን የልማት አውታር አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል። የማዳበሪያ አቅርቦት በተሳካ ሁኔታ እንዲደርስ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ገለጹ።
Next articleኢትዮጵያ እና ጣሊያን በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና ባለብዙ ወገን ጉዳዮች ዙሪያ መከሩ።