
ባሕር ዳር: ጥር 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2016 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከማዕድን ወጪ ንግድ 142 ነጥብ 978 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የማዕድን ሚኒስቴር አስታውቋል።
በስድስት ወሩ ሶስት ነጥብ 51 ሚሊየን ቶን ሲሚንቶ መመረቱም ተመላክቷል።
ማዕድን ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት የስድስት ወር የዕቅድ አፈጻጸምን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየገመገመ ነው።
በወቅቱ የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ እንደገለጹት፤ በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡ የማዕድናት ምርት ሽያጭ 243 ነጥብ 24 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 142 ነጥብ 978 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል።
ገቢው የተገኘው ወርቅ፣ ታንታለም፣ ሊቲየም ኦር፣ ጌጣጌጥና የኢንዱስትሪ ማዕድናትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኢፕድ እንደዘገበው በ2016 በጀት ዓመት ስራ ላይ ያሉት 11 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች መሆናቸውን ገልጸው፤ ፋብሪካዎች በዓመት 14 ሚሊየን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል።
ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ሲሚንቶ ፍላጎት 36 ሚሊየን ቶን ነው ያሉት ሚንስትሩ፤ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ሶስት ነጥብ 51 ሚሊየን ቶን ሲሚንቶ ተመርቷል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!