የወደብ ግንባታውን ተከትሎ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት ላይ ማተኮር እንደሚገባ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡

102

የወረታ ከተማን እድገት ለማሻሻል እና ነዋሪዎቿን ተጠቃሚ ለማድረግ ሕዝቡ እና መንግስት በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ ለአብመድ አስተያዬት የሰጡ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የደረቅ ወደብ ተርሚናሉን ከመገንባቱም በፊት ወረታ ሥሪቷ የደረቅ ወደብ ይመስል ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ- ባሕር ዳር-ጎንደር-መተማ-ሱዳን ወይም ከባሕር ዳር-ደብረ ታቦር-ወልድያ-መቀሌ ለሚደረግ ጉዞ ሁሉ ማለፊያ ናት፡፡ ከባሕር ዳር ከተማ በቅርብ ርቀት፣ ከጣና ሐይቅ ጎን መገኘቷ ደግሞ ከተማዋን ለዘርፈ ብዙ የንግድ እንቅስቃሴ ተመራጭ ያደርጋታል፡፡

በአካባቢው በስፋት የሚመረተው ሩዝ እና አትክልትና ፍራፍሬም ሌላው የከተማዋ የንግድ ተፈላጊነት ማሳያ ነው፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ስምንተኛውን የደረቅ ወደብ ተርሚናል የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ አጠናቅቆ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ይህንን ተከትሎም የከተማዋ የንግድ ተመራጭነት እየጨመረ መጥቷል ብለዋል አብመድ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች፡፡ በወረታ ከተማ የሆቴል አገልግሎት ዘርፍ የተሰማራው ወጣት ሰይድ ክብረት እንደተናገረው የደረቅ ወደቡ ግንባታ በከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ አንፃራዊ ለውጥ መፍጠር ጀምሯል፡፡

አሁን ካለበት የግንባታ ወቅት ጀምሮ ከዝቅተኛው የጉልበት ሠራተኛ እስከ “ትራንስፖርት” እና የሆቴል ዘርፍ የተሰማሩ አገልግሎት ሰጪዎች ተጠቃሚዎች ናቸው፤ በርካታ ወጣቶችም ጊዜያዊ የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ አሁን ላይ እየታየ ያለውን አንፃራዊ ተጠቃሚነት ዘላቂ ለማድረግ እና ከተማዋን ለማሳደግ ነዋሪዎቹ፣ የከተማ አስተዳደሩ እና መንግስት በትኩረት መሥራት ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ወጣት ሰይድ አስተያየት ሰጥቷል፡፡ ወጣቶቹ እና ነዋሪዎቿ የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፤ የከተማ አስተዳደሩ ከባለሃብቶች ጋር ተቀራርቦ መነጋገር፣ መንግስት ደግሞ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው ነው አስተያየት የሰጠው፡፡

በተለይም በከተማዋ ያለው ብቸኛ መንገድ ባለአንድ መስመር በመሆኑ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ስላለ አካፋይ መስመር ሆኖ እንዲሠራ የከተማዋ ነዋሪዎች የበርካታ ዓመታት ጥያቄ እንደሆነም ተመላክቷል፡፡ የመስመር ዳር መብራቶች እና የሆቴል ግንባታ ፈቃድም አፋጣኝ ምላሽ ያስፈልጋቸዋል፡፡

የወረታ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ታደለ ሙጨ ደግሞ የደረቅ ወደቡ ግንባታ ለከተማዋ ተጨማሪ ዕድል ይዞ መጥቷል ነው ያሉት፡፡ ይህን ዕድል በዘላቂነት ለመጠቀም የከተማ አስተዳደሩ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የመንገዱን ችግር ለመፍታት በወደቡ ምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ለትራንስፖርት ሚኒስትሯ ጥያቄውን ማቅረባቸውን ከንቲባው ተናግረዋል፡፡ ሚኒስትሯ ችግሩን በአካል በመመልከታቸውም በቅርቡ ምላሽ ያገኛል የሚል እምነት እንዳላቸው ነው ከንቲባው የተናገሩት፡፡

ለሆቴል እና መሰል አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች የግንባታ ፈቃድ መስጠትን በተመለከተም ባለአንድ እና ባለሁለት ኮከብ ሆቴል ቦታ በሊዝ የሚመራ በመሆኑ በቅርቡ ጨረታ እንደሚወጣ አስታውቀዋል፡፡ ለባለሦስት እና ባለአራት ኮከብ ሆቴሎች ግንባታ ፈቃድ በክልል የሚሰጥ በመሆኑ እና በርካታ የንግድ ፈቃድ ንድፈ ሃሳብ ስለቀረበ ክልሉ በተለየ ሁኔታ እንዲያስተናግድላቸው እየጠየቁ መሆኑንም አቶ ታደለ ነግረውናል፡፡ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የአካባቢውን ፀጋዎች በማስተዋወቅ እና በንግድ እንቅስቃሴ መስፋፋት ላይ መልካም ዕድል እንዳለው የሚጠበቀው የወረታ ደረቅ ወደብ ግንባታ ለቀጣናው የንግድ ትስስርም ፋይዳው የጎላ እንደሚሆን ታምኖበታል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Previous articleዶክተር አሚር አማን በሥጦታ ያገኙትን 1 ሚሊዮን ብር ለሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን አበረከቱ፡፡
Next articleየወደብ ግንባታውን ተከትሎ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት ላይ ማተኮር እንደሚገባ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡