የወሎ ማዕከል የተሃድሶ ሠልጣኞች ጥያቄያችንን በሰላማዊ ትግል ለማስመለስ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ መቀበላቸውን ገለጹ፡፡

23

ደሴ: ታኅሳስ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሰላም ጥሪውን ተቀብለው በወሎ ማዕከል ለተሃድሶ ሥልጠና የገቡ ታጣቂዎች የዞን እና የክልል የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን በሰላማዊ ትግል መፍታት የሚቻልበት ሁኔታ እንደሚኖር በማመን ከትጥቅ ትግል አማራጭ ተመልሰናል ብለዋል ተጣቂዎቹ፡፡ ወንድም ከወንድሙ ጋር በመጋጨት የሚመለስ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ እንደማይኖር የገለጹት አስተያየታቸውን የሠጡ ታጣቂዎች ሁሉም ለዚሁ የሰላም ትግል የበኩሉን መወጣት እንደሚገባው ነው የገለጹት፡፡ ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት መኾኑንም መገንዘባቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በእለቱ ለታጣቂዎቹ ማብራሪያ የሰጡት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን የአማራ ሕዝብ በሰሜኑ ጦርነት ከደረሰበት ጉዳት ሳያገግም ዳግም ጦርነት ውስጥ በመግባቱ በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አስታውሰዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ የታወቁ ጥያቄዎች እንዲመለሱ በመንግሥት በኩል በርካታ ሥራዎች እየተከናዎኑ መኾኑን ነው ዋና አስተዳዳሪው ያብራሩት፡፡ ጥያቄዎቹ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በትብብር የሚፈቱ መኾናቸውን ጠቅሰው የትጥቅ ትግል አማራጭ ጥቄዎቹን የበለጠ የሚያወሳብ እና የክልሉን ሕዝብ ኢኮኖሚ የሚያደቅ በመኾኑ ይህን አማራጭ ያደረጉ ኃይሎች የሰላም ጥሪውን አሁንም እንዲጠቀሙበት ጠይቀዋል፡፡ ጥሪውን የተቀበሉ አካላት ከሥልጠና በኋላ ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለው ሕይዎታቸውን በአግባቡ የሚመሩበት ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀን አምባቸው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleክስ የመስማት እና ውሳኔ የመስጠት ተግባር በአዲስ (ልዩ ፍርድ ቤት) ሊከወን ይገባል ተባለ።
Next articleበአማራ ክልል የሚገኙ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቅርቡ የተማሪ ጥሪ እና የመማር መሥተማር ሥራ እንደሚጀምሩ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።