ቻይና የበረሃ አንበጣ መንጋ ለመከላከል የሚያስችሉ 100 ሺህ ዳክዬዎችን አሰማራች፡፡

380

ባሕር ዳር፡ የካቲት 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) በኮሮና ቫይረስ እየታመሰች ላለችው ቻይና የበረሃ አንበጣ መንጋም ሥጋት ደቅኖባታል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ ቻይናን አስግቷታል፡፡ “የአንበጣ ወረርሽኙ” በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ቻይና ከሕንድ እና ፓኪስታን ጋር ከምትዋሰንበት ዥን ጂያንግ ግዛት ድንበር እንደደረሰ ታውቋል፡፡

ይህም በኮሮና ቫይረስ እየታመሰች ላለችው ቻይና ሌላ ፈተና ደቅኖባታል፡፡ በመሆኑም በሀገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ መንጋ ‹‹ለመከላከል ያስችለኛል›› ያለችውን መፍትሔ እየተጠቀመች ነው፡፡ ለዚህም ከድንበሮቿ አካባቢ ሆነው መንጋውን የሚከላከሉ 100 ሺህ ዳክዬዎችን ማሠማራቷን አስታውቃለች፡፡

‘እሾህን በእሾህ’ እንዲሉ ቻይና ያሠማራቻቸው የዳክዬ ወታደሮች የበረሃ አንበጣ መንጋውን እያሳደዱ መመገብ ጀምረዋል፡፡ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ባሰባሰቡት አስተያዬትም በመከልከሉ ሥራ ዳክዬዎች ከጸረ ተባይ ኬሚካሎች በተሻለ መልኩ ውጤታማ ሆነዋል፡፡ በምን ህል ጊዜ እንደሆነ ባይገልጹትም አንድ ዳክዬ በአራት ሜትር ካሬ መሬት ላይ ያረፈ አንበጣን ማጽዳት እንደሚችል ነው የተዘገበው፡፡

በአንበጣ መንጋው የተነሳ ከፍተኛ ችግር ውስጥ የገባችው ፓኪስታን በሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ አውጃለች፡፡ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካህን አደጋውን “ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ ያልታዬ አስከፊ ወረርሽኝ” ብለውታል፡፡

መነሻውን ከየመን በማድረግ በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም በኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሥጋት የፈጠረው የበረሃ አንበጣ መንጋ የሩቅ ምሥራቅ ሀገራትንም ተመሳሳይ ሥጋት ውስጥ ከትቷል፡፡

ምንጭ፡- ሲ ጂ ቲ ኤን እና ግሎባል ታይምስ

በአስማማው በቀለ

Previous articleኤርትራዊቷን ‘ሞቴን ጎንደር ያድርገው’ ያሰኛት ምን ድን ነው?
Next article‹‹የኅብረተሰቡን ችግሮችን ለመፍታት በየተቋማቱ የሚካሄዱ ጥናቶች ከመደርደሪያቸው ወርደው ወደ ተግባር መለወጥ አለባቸው።›› የውይይቱ ተሳታፊዎች