
ቻግኒ ከተማ ውስጥ 62 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የፕላስቲክ ከረጢት ፋብሪካ ዛሬ ተመርቋል።
ፋብሪካው በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አሥተዳድር በቻግኒ ከተማ አሥተዳድር ነው የሚገኘው። አቶ እሱእንዳለ ሽመልስ በተባሉ ባለሀብት ተገንብቶ ወደ ሥራ የገባው ፋብሪካ በ5 ሺኅ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ነው።
በአሁኑ ወቅት ለ231 ሰዎች የሥራ እድል እንደፈጠረም የቻግኒ ከተማ አሥተዳድር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ የኔው ምኅረት ለአብመድ ገልፀዋል። በሙሉ የማምረት አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ ደግሞ ለ400 ሠራተኞች የሥራ እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል።
እንደ አቶ የኔው ገለፃ በቻግኒ ከተማ አሥተዳድር በአጠቃላይ 56 ፕሮጀክቶች መሬት ወስደው ወደ ግንባታ ገብተዋል። ከእነዚህ ውስጥ የዛሬውን ጨምሮ ዘጠኙ ወደ ማምረት ገብተዋል። 14 ደግሞ ግንባታቸውን አጠናቅቀው ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።
ለማምረት የሚያስችሉ ቁሳቁስ እና መብራት እንደተሟላላቸው ወደ ሥራ እንደሚገቡም ነው የከተማ አሥተዳድሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊው የተናገሩት። የከተማ አሥተዳድሩ የመብራት ችግሩን ለመቅረፍ ከባለሀብቶች ጋር በትብብር እየሠራ መሆኑን የተናገሩት አቶ የኔው አሁን ላይ ለዚሁ ሥራ ከ445 ሺህ በላይ ብር መመደቡንም ገልፀዋል።
በቻግኒ ከተማ አሥተዳድር ውስጥ እስካሁን ወደ ማምረት የገቡት ፕሮጀክቶች ለ319 ሰዎች ቋሚ፣ ከ3 ሺኅ በላይ ለሚሆኑት ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደፈጠሩ ታውቋል።
ዘጋቢ፦ አስማማው በቀለ
ፎቶ፦ ከአዊ ኮሚዩኒኬሽ