ኬንያ ከፍተኛ የደም እጥረት አጋጠማት፡፡

75

ባሕር ዳር: የካቲት 08/2012 ዓ.ም (አብመድ) በውጭ ሀገራት ድጋፍ ላይ የተንጠለጠለው የኬንያ የደም ልገሳ መርሀ ግብር ችግር አጋጥሞታል፡፡

ኬንያ በሆስፒታሎቿ ውስጥ የደም እጥረት ገጥሟታል፡፡ በዚህም የተነሳ አማራጩ ከህሙማን ዘመዶች ወይም ጓደኞች ደም እንዲለገስ ማድረግ ሆኗል፡፡ መፍትሔው ግን የደም ለጋሾች ቁጥር ከጠቅላላ የሕዝብ ቁጥር ጋር የተመጣጠነ እንዲሆን ማድረግ ነው ብሏል የዓለም የጤና ድርጅት፡፡

እንደ ድርጅቱ መረጃ ችግሩን ለማቃለል ኬንያ በዓመት 1 ሚሊዮን ዩኒት ደም መሰብሰብ አለባት፡፡ ከ47 ሚሊዮን ሕዝቦቿ ውስጥ 1 በመቶዎቹ ብቻ ደም ቢለግሱ እንኳን 470 ሺህ ዩኒት ደም መሰብሰብ ትችላለች ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ አንድ ዩኒት ደም የሦስት ሰዎችን ሕይወት ያተርፋል በሚለው ሥሌት መሠረት ከ1 ሚሊዮን 4 መቶ ሺኅ በላይ ሰዎችን ከሞት ይታደጋል፡፡

ነገር ግን እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2018/2019 የተሰበሰበው የደም መጠን 164 ሺኅ ዩኒት ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከሚያስፈልገው እና በዓለም የጤና ድርጅት ከተቀመጠው መስፈርት በጣም ያነሰ ነው፡፡ በመሆኑም በኬንያ የደም ለጋሾችን ቁጥር ማሳደግ እንደሚገባ ነው የተመላከተው፡፡

በኬንያ ከፍተኛ የደም ለጋሾች ቁጥር የተመዘገበው እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ሥሌት በ2018 ነበር፡፡ በወቅቱ 77 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ሕዝብ ደም እንደለገሰ ዘገባው አስታውሷል፡፡

እንደ የሀገሪቱ መንግሥት መረጃ በኬንያ የደም ልገሳ መርሀ ግብር የሚካሄደው ከወጭ ሀገራት በሚገኝ ድጋፍ ነው፡፡ 80 በመቶ የሚሆነው ድጋፍም ከውጭ ሀገራት ለጋሾች የተገኘ ነው፡፡ ዋነኛው የሀገሪቱ ለጋሽ “ፔፕፋር” ተብሎ የሚጠራው በአሜሪካ መንግሥት ኤች አይ ቪን ለመዋጋት የሚውል የበጎ አድራጎት ዘርፍ ነው፡፡

ኬንያም የዚህ ድጋፍ ዋነኛ ተጠቃሚ ናት፤ ነገር ግን ድጋፉ ካሳለፍነው መስከረም ጀምሮ ስለተቋረጠ የደም ልገሳ መርሀ ግብሩ እና ለልገሳው የሚውለው ቁሳቁስ ሙሉ በሙሉ እንደተቋረጠ ነው የተገለጸው፡፡ የኬንያ ብሔራዊ ሸንጎ አባል ሩዌይዳ ኦቦ ችግሩ የተከሰተው መርሀ ግብሩ በውጭ ድጋፍ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ድጋፉ ሲቋረጥ መንግሥት የሚወስደው አማራጭ የመፍትሔ እቅድ እንደሌለውም ነው የገለጹት፡፡

ምንጭ፡- ቢቢሲ

በብሩክ ተሾመ

ትኩስና ተከታታይ መረጃዎችን ለማግኘት በእነዚም አማራጮች ይከታተሉን፡፡
ቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዮቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC

Previous articleናይል ማራቶን ዓለም አቀፋዊ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ፌዴሬሽኑ አስታወቀ።
Next article“ትምህርት ቤቱ ሰራዊቱ ለሕዝቡ ቋሚ ሀውልት ያስቀመጠበት ነው።” ጀነራል አደም መሀመድ (የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም)