
ባሕር ዳር: የካቲት 08/2012 ዓ.ም (አብመድ) የባሕር ዳሩ “ናይል ማራቶን” ዓለማቀፋዊ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ናይል ማራቶን ዛሬ የካቲት 8/2012 ዓ.ም በባሕር ዳር ተካሂዷል። ላለፉት ስምንት ዓመታት “የባሕርዳር ከተማ ሩጫ” በመባል ይካሄድ የነበረው ሩጫ ዘንድሮ ሥያሜው “ናይል ማራቶን” ወደ ሚል ሥያሜ ተቀይሮ ለ9ኛ ጊዜ ተካሂዷል። መነሻ እና መድረሻውን አዝዋ ሆቴል በማድረግ የተካሄደው ሩጫ 10 ሺህ ሜትር ሸፍኗል። በውድድሩ በወንዶች፣ ጊዜው አበጀ ከአዲስ አበባ መብራት ኃይል አንደኛ ሲወጣ፣ ሀይማኖት ማተብ ከኢትዮጵያ ሆቴል ሁለተኛ ወጥቷል። ሦስተኛ ደረጃ የያዘው ደግሞ በረከት ዘለቀ ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ነው፡፡
ከሴቶች አንችንአሉ ደሴ ከኢትዮጵያ ሆቴል አንደኛ ወጥታለች። በግል የተወዳደረችዋ ዓለምአዲስ እያዩ ሁለተኛ ስትወጣ ትዕግስት ጌትነት ከአማራ ማራሚያ ቤቶች ሦስተኛ ደረጃ ይዛለች።
በውድድሩ የባሕር ዳር ከተማ የውበት አባት እየተባሉ የሚጠሩት አቶ ዋሴ አካሉ ልዩ ተሻላሚ ሆነዋል። አቶ ዋሴ አካሉ ለባሕርዳር ከተማ ልዩ ውበት ያጎናፀፋትን ዘንባባዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በመትከል የሚታወቁ የከተማዋ ባለውለታ እና የውበቷ ምንጭ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል። በናይል ማራቶንም የክብር ካባ ተበርክቶላቸዋል። የናይል ማራቶን ሥራ አስኪያጅ አትሌት መልካሙ ተገኘ ውድድሩ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን እርስ በርስ አንዲያገናኝና ዓለማቀፋዊ እንዲሆን ለማድረግ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል። ውድድሩ ሙሉ ማራቶን ሆኖ ዓለማቀፍ አትሌቶች እንዲገኙበት እንደሚደረግም አስታውቀዋል፡፡
በውድድሩ የተገኙት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ የቀድሞውን የባሕር ዳር ከተማ ሩጫ እንደመሠረቱ አስታውሰው ውድድሩ በፈለጉት ልክ አለማደጉን ተናግረዋል። ማራቶኑ ዓለምአቀፋዊ እንዲሆን ከከተማ አስተዳድሩ እና ከክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ጋር እንደተነጋገሩም ገልፀዋል። እንደ ሌሎቹ ስመ ጥር የማራቶን ውድድሮች ታዋቂ፣ ሽልማቱም ዓለም አቀፋዊ መሆን አለበት ነው ያሉት አቶ ቢልልኝ።
ዛሬ የተሳተፈው ሰው በሚጠበቀው ልክ አይደልም ያሉት አቶ ቢልልኝ ስፖርት ፋይዳው ለሰላም፣ ለፍቅርና ለአንድነት በመሆኑ ሕዝቡ ወደፊት መሳተፍ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡ እንዲህ አይነት ውድድሮች ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ትልቅ እድል ስለሚሰጡ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፡፡
ናይል ማራቶን ከፍ ባለ ደረጃ አንዲጠራ የመንግስት አካላትም ተሳትፈውበት በሰፊው መሠራት እንዳለበትም አቶ ቢልልኝ ተናግረዋል፡፡ ማራቶኑ ዓለምአቀፋዊ እንዲሆን ፌዴሬሽኑ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።
የባሕርዳር ከተማ አስተዳድር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መሐሪ ታደሰ (ዶክተር) የናይል ማራቶን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመነጋገር ጉዞ እንደጀመረ፣ በእውቀቱ የበለጸገ፣ በአካላዊ ብቃቱም የጠነከረ፣ የሥራ ተነሳሽነት ያለው፣ በማንነቱ የሚኮራ ጠንካራ ትውልድ ለመገንባትም እንዲህ አይነት ውድድር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሩጫው ከከተማዋ አልፎ ዓለምአቀፋዊ የሩጫ መድረክ እንዲሆን ጥረት እንደሚደረግም ነው ዶክተር መሐሪ የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ