ያልዘመነው የቱሪዝም ዘርፍ ዜጎች ይበልጥ እንዳይጠቀሙ አድርጓል፡፡

209

ባሕር ዳር: የካቲት 07/2012 ዓ.ም (አብመድ) የቱሪስት መዳረሻዎች የአለባበስ ደንብ አለመኖር፣ ለብዙዎች ሊፈጠር የሚችለውን የሥራ ዕድል ነፍጓል፡፡

በሀገሪቱ ያሉት ተፈጥሯዊም ሆኑ ሰው ሠራሽ የመሥህብ ሀብቶች የጎብኝዎች መዳረሻ በመሆን ለአካባቢ እና ለሀገር ገቢ ያስገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ ሀገርን ይበልጥ ሊያስተዋውቅ የሚችል አሠራር ተግባራዊ አለመደረጉ ለመግቢያ ወይም በአካባቢዎቹ ሲቆዩ ለአገልግሎት ከሚከፍሉት ገንዘብ ያለፈ ገቢ ከጎብኝዎች እንዳይገኝ አድርጓል፡፡ ይህም ለብዙዎች የሥራ ዕድል ሊፈጥር የሚችልን ገንዘብ እያስገኘ አይደለም፣ ሀገርንም ይበልጥ ለማስተዋዎቅ የሚያስችሉ ዕድሎችን አሳጥቷል፡፡

በሀገሪቱም ሆነ በአማራ ክልል በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች የአለባበስ ደንብ አለ ወይ? በማለት አብመድ ባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎችን እና የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ባለሙያዎችን አነጋግሯል፡፡ አብመድ ካነጋገራቸው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ አንበሴ ግርማው ‹‹ቅርሶችን ለመጎብኘት የአለባበስ ደንብ አለመኖሩ የዜጎችን ጥቅም ያላስከበረ፣ ከሳይንሳዊ አሠራር ይልቅ ዘልማዳዊ አሠራርን ያስቀጠለ ነው›› የሚል ሀሳብ አላቸው፡፡ የቱሪዝም ተቋማቱ ከዘርፉ አዳዲስ የገቢ ምንጮችን እየፈለጉ የማስተግበር ውስንነት እንዳለባቸውም ትዝብታቸውን አጋርተውናል፡፡ በሁሉም የጎብኝዎች መዳረሻዎች አካባቢ ወጥነት ያለው የአለባበስ ደንብ በማስተግበር ሕዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ሌላኛዋ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ስመኝ ይሁኔ የቱሪዝም አለባበስ ደንብን በተመለከተ መኖሩንም ሆነ አለመኖሩን ከዚህ በፊት እንደማታውቅ አስታውሳ ቢሠራበት ሌላ ትልቅ የገቢ ዘርፍ እንደሚሆን ተናግራለች፡፡ በሁሉም የጎብኝዎች መዳረሻዎች የባህል አልባሳትን ጨምሮ ከየአካባቢዎቹ የሚሠሩ ልዩ ውበትን የሚገልጹ እንደ ጫማ፣ ኮፍያ የመሳሰሉ ልዩ ልዩ መገለጫዎችን እንዲጠቀሙ ማድረግ አልባሳቱን ከማዘጋጀት እስከ መሸጥ ባሉት ሂደቶች ለብዙዎቹ ወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ አካባቢዎችንም ይበልጥ ለማስተዋዎቅ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ግን መቼ ይተግበር? ማንስ ያስተግብረው?

የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የባሕል እሴቶች ልማት ባለሙያ አቶ አዝመራው በየነ ከቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች እስከ አሁን የአለባበስ ደንብ ወይም መመሪያ አለመዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ በቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ላይ የሚታየው የተዘበራረቀ አለባበስ የቅርሶችን ውበት ካለማጉላቱም በላይ ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን ጥቅም እያስገኘ ባለመሆኑ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም የአለባበስ ደንብ እንዲኖረው በዕቅድ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ ዕቅዱ ከመቼ ጀምሮ እንደሚታቀድና እንደሚተገበር ግን የተጨበጠ ሀሳብ አላቀረቡም፡፡

በኢትዮጵያ 80 በመቶ የሚሆነው ጎብኝ መዳረሻው አማራ ክልል ነው፡፡ ከዚህ በፊት ወደ ቅርሶች ለመግባት ከሚከፍሉት ገቢ ውጭ መዳረሻዎቹ ሌሎች የገቢ አማራጮችን እየተጠቀሙ አይደለም፤ ይህ ደግሞ ለአካባቢው ኅብረተሰብም ሆነ ለመንግሥት የሚገባውን ገቢ ማግኘት እንዳላስቻላቸው አስታውሰዋል፡፡ ‹‹አሁን ግን ከሕዝቡም ሆነ ከአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የመጣውን በቱሪስት መዳረሻዎች የአለባበስ ደንብ እንዲኖር የሚመክረውን ሀሳብ በተግባር ላይ ለማዋል እንሠራለን›› ብለዋል አቶ አዝመራው፡፡

በመሆኑም በአማራ ክልል በበሚገኙት ቅርሶችና የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች እንደየአካባቢያቸው ማኅበረሰቡን የሚወክሉ አለባበሶችን ተቋማቸው እንደሚተገብር ዕምነት እንዳላቸው ነው አቶ አዝመራው የተናገሩት፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

Previous articleየኮሮና ቫይረስ ግብጽ መግባቱ ተረጋገጠ፡፡
Next articleየገዳሪፍ ክፍለ ግዛት ልዑክ በባሕር ዳር ፋብሪካዎችን እየጎበኘ ነው፡፡