
ልዑኩ ጎንደር ከተማ ሲደርስ የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ማስተዋል ስዩምና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውለታል።
የገዳሪፍ ክፍለ ግዛት ዋና አስተዳዳሪ እና ልዑካቸው ነገ ቅዳሜ የካቲት 7/2012 ዓ.ም የወረታ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ምረቃ መርሀ ግብር ላይ እንደሚታደሙ ይጠበቃል።
በመርሀ ግብሩ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ፣ የክልሉና የፌዴራል የሥራ ኃላፊዎች እንደሚገኙ ነው የሚጠበቀው።
ነገ ከሰዓት እና እሁድ ደግሞ የአማራ ክልል የሥራ ኃላፊዎች እና የገዳሪፍ ክፍለ ግዛት ልዑክ የጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ በባሕር ዳር ይመክራሉ፤ መሠረተ ልማቶችንም ይጎበኛሉ።
ኢትዮጵያ በአማራ ክልል በኩል፣ ሱዳን ደግሞ በገዳሪፍ ክፍለ ግዛት ሰፊ ወሰን ይጋራሉ። የአማራ ክልል እና የገዳሪፍ መሪዎችም በድንበር አካባቢ ፀጥታን ለማስከበር፣ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቆጣጠር እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች በጋራ ለመሥራት በየጊዜው እየተገናኙ እንደሚመክሩ ይታወቃል።
ዘጋቢ፦ ፍጹምያለምብርሃን ገብሩ