
ባሕር ዳር: የካቲት 06/2012 ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ከየትኛውም አካል ተጽዕኖ ቢኖርም ብሄራዊ ጥቅሟን ያላሰጠበቀ ስምምነት እንደማትፈርም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ የካቲት 6/2012 ዓ.ም መግለጫ ሰጥተዋል። በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ እየተደረጉ ያሉት ውይይቶች ጉዳይ በመግለጫው ትኩረት ከተሰጣቸው ነጥቦች መካከል አንዱ ነው፡፡
ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲ.ሲ ሲያደርጉት የነበረውን ድርድርና የረቂቅ የስምምነት ሰነድ ዝግጅት ሳይቋጭ መጠናቀቁ ይታወቃል።
ቃል አቀባዩ አቶ ነቢያት በሰጡት ማብራሪያ በግድቡ ዙሪያ ከየትኛውም አካል ተጽዕኖ ቢኖር ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን አሳልፋ እንደማትሰጥና መርህ ላይ የተመሠረተ ጥቅሟን ያስጠበቀ ድርድር እንደምታራምድ አረጋግጠዋል ሲል ኢ.ፕ.ድ ዘግቧል።
በዋሽንግተን ዲ.ሲ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ለማዘጋጀት ሲካሄድ የነበረው ውይይት በዚህኛውም ዙር ሳይቋጭ ትናንት ማማምሻውን መጠናቀቁ ይታወሳል።