ከሀገራዊ አንድነት እስከ ይቅርታና ፍቅር ማወጃነት፤ ደረስጌ ማርያም፡፡

513

በሰሜን ጎንደር ዞን ጃናሞራ ወረዳ የምትገኘው ደረስጌ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከ165 ዓመታት በፊት አጼ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ተብለው የተቀቡባትና የዘመነ መሳፍንትን መከፋፈክ ታሪክ ዘግተው ኢትዮጵያዊ አንድነትን ያወጁባት ታሪካዊ ቦታ ናት፡፡ ‹ስሜን ስሜን ላይ እነግርሃለሁ›› ሲሉ የነበሩት ደጃች ካሳ ኃይሉ በደጃች ውቤዋ ደረስጌ ማርያም ላይ የካቲት 5 ቀን 1847ዓ.ም ነበር ንግሥናቸውን አውጀው ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ የተባሉት፡፡

የአጼ ቴዎድሮስን የንግሥና መታሰቢያ ቀን በማስመልከት በደረስጌ ማርያም አጸድ ዘንድሮም ጥላቻንና በቀልን በማውገዝ አንድነትና ፍቅር ታውጇል፡፡ በደረስጌ ማርያወም በተካደው ሥነ ሥርዓት በጃናሞራ ወረዳና አካባቢው በግለሰቦች መካከል አልፎ አልፎ በሚከሰቱ ግላዊ ግጭቶች የዜጎች ሕይወት እንዳይቀጠፍ በፅኑ ተወግዟል፡፡


በአካባቢው አልፎ አልፎ በሚከሰቱ ግጭቶች እስከ ሕይወት መጥፋት የሚያደርሱ ጥፋቶች ደርሰው ያውቃሉ፤ ደም የመመላለስ እና የማያባራ ጥል ውስጥ መግባት በአካባቢው በተወሰነ መልኩ የሚታዩ ችግሮች ነበሩ፡፡ በዚሁ ዝግጅት ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የጅማ እና ሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ እስጢፋኖስ እንዲሁም የአውስትሪሊያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ጴጥሮስ እና በአካባቢው የሚገኙ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ተገኝተው የተቀያየሙ ይቅር ተባብለዋል፤ ድጋሜ ቂም በቀል እንዳይኖርም ከእርቀ ሠላም በኋላ ተወግዟል፡፡


በዝግጅቱ ከዚህ በኋላ ደም ያፈሰሰ ከማንኛውም ማኅበራዊ ተሳትፎ እንዲታገድ፣ ሕይወቱ ሲያልፍ እንኳ ተገቢው ማኅበራዊ ክብር እንዳይደረግለትና ሌሎችም ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብሮች እንዲነፈጉት ውግዘት ተላልፏል፡፡ በዕለቱ በተለያዩ ጊዜያት ደም የተቃቡ 52 ቤተሰቦች ተገኝተው ለወደፊቱ በደም ላይፈላለጉና እርስ በእርስ ላይገዳደሉ በጳጳሳቱ ፊት ቃል ገብተዋል፡፡


የዝግጅቱ አስተባባሪ ‹ጃን የትምህርትና ልማት ድርጅት› በቀጣይ ቂም በቀልና ጥላቻን ለመቀነስና አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ ለማድረግ ከወረዳ እስከ ቀበሌ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከመስጂዶችና አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶ ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ የድርጅቱ ኃላፊ አቶ ባያብል ሙላቴ እንደገለጹት በአካባቢው ቀጣይ ደም መፋሰስ እንዳይኖር መዋቅር በመዘርጋትና ማኅበራዊ ስምምነት እንዲጠናከር ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡


የሰሜን ጎንደር እና ጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ እስጢፋኖስ ደግሞ በዚህ የሀገር ሠላም አሳሳቢ በሆነበት ወቅት ሠላምን የሚሰብክ መርሀ ግብር መዘጋጀቱን አድንቀው ለሀገር አንድነት በለፉት ንጉሥ የንግሥና መታሰቢያ ቀን መሆኑ ልዩ እንደሚደርገው ጭምር አስታውቀዋል፡፡ ብጹእነታቸው ለጃናሞራ ሕዝብ ባስላለፉት መልዕክት ‹‹ጥንት የሀገር አንድነትን አሁን ደግሞ የሀገር ሠላምን ለማወጅ በመታደላችሁ ደስ ሊላችሁ ይገባል›› ብለዋል፡፡


የእስልምና ሃይማኖት ተወካዮችን ወክለው ንግግር ያደረጉት አቶ ሙሉጌታ ዓለሙ ‹‹የትኛውም ሃይማኖት መገዳደልን ይፀየፋል፤ አማኞች ሆነን ሳለ ስለምን ደም እንቃባለን?›› ሲሉ ጠይቀዋል፤ ተገቢ አለመሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ ‹ደም አድርቅ› በሚል ማዕረግ የሚንቀሳቀሱ የሀገር ሽማግሌዎች ግጭቶች እንዲቀንሱ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰው ውግዘቱ ከቤተ ክርስቲያኗ መተላለፉ ለሀገር ሽማግሌዎቹ ሥራቸውን እንደሚያቀልላቸው ለአብመድ ገልፀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ስማቸው ማሩ -ከጃናሞራ
ፎቶ፡- ከባያብል ሙላቴ ገጽ

Image may contain: 9 people, people standing and crowd
Previous articleየኤክሳይዝ ታክስ አዋጁ ምን ምን ጉዳዮችን ይመለከታል?
Next articleየሀገራቱ አቋምም ሆነ የሌሎች ተጽእኖ ብሔራዊ ጥቅምን አሳልፎ የሚሰጥ ድርድር ውስጥ እንደማያስገባ ሚኒስቴሩ አስታወቀ፡፡