አስፈሪውን የኦልድትራፎርድ ግርማ ሞገሥ ማን ይመልሰው?

116

ባሕር ዳር: ኅዳር 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ 20 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት የደመቀ ታሪክ ባለቤት ነው፤ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግም አራት ዋንጫዎችን አንስቷል ማንቸስተር ዩናይትድ።
ዘ ኢዱኬሽናል የተሰኘ መጽሔት ባወጣው መረጃ መሰረት ዩናይትድ ከሪያል ማድሪድ በመቀጠል የዓለማችን ተወዳጅ ክለብ ነው።
ክለቡን በኢንስታግራም የሚከተሉት ከ41 ሚሊዮን በላይ የእግር ኳስ አፍቃሪያን ከማድሪድ በመቀጠል ሁለተኛው ትልቅ ቁጥር ነው።
ማንቸስተር ዩናይትድ ይሄን ዝና እና ተወዳጅነት ያገኘው በውጤታማው አሠልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ዘመን በነበረው የበላይነት ነው።
በተጋጣሚዎቹ የሚፈራ፤ በደጋፊዎቹ ደግሞ ደረት የሚነፋበት ነበር ኦልድትራፎርድ በፈርጌ ዘመን።

አሁን ቆፍጣናው አሠልጣኝ ከነገሡበት የአሠልጣኝነት ሥራ በጡረታ ከተሰናበቱ ዓመታት ተቆጥረዋል። አስፈሪው የኦልድትራፎርድ ግርማ ሞገሥ ከቀለለም ተመሳሳይ ጊዜያት ነጉደዋል።
ዩናይትድ ፈርጉሰንን በጡረታ ካጣ በኃላ በ10 ዓመታት ውስጥ አምስት ቋሚ እና ሦስት ጊዚያዊ አሠልጣኞችን ቀጥሯል። ሰባቱ አሠልጣኞች ክለቡን የሚመጥን ሥራ መሥራት አቅቷቸው በአጭር የጹሑፍ መልዕክት ከትልቁ ክለብ ተሰናብተዋል።
ተረኛው ቲንሃግም እነሞሪንሆንን የጠራረገው ጎርፍ በብዙ እያንገላታቸው ነው፤ እንዲያውም ተኪያቸው አየተፈለገ መኾኑን ዘገባዎች ጭምጭምታውን ከነገሩን ውለው አድረዋል።
ዴቪድ ሞይስ ፈርጉሰንን የተኩ የመጀመሪያው አሠልጣኝ ነበሩ። “የተመረጡት” ይሏቸዋል የዩናይትድ ደጋፊዎች በፈርጉሰን አልጋ ወራሽ ተደርገው መመረጣቸውን ለመግለጽ።
በፈርጉሰን የታመኑት ሞይስ ግን ዩናይትድን ቁልቁል አምዘግዝገውታል። ክለቡ ትንንሽ በሚባሉ ክለቦች ሳይቀር በሜዳው በመሸነፍ ለተጋጣሚዎች የቀለለ ኾነ።
ይህን ተከትሎ አሠልጣኙ ከ10 ወራት ቆይታ በኃላ ተባረዋል። ከሰር አሌክስ በኃላ ዩናይትድን ካሠለጠኑ አሠልጣኞች ትንሽ ነጥብ የሰበሰቡ የሚል የማይፈልጉትን ታሪክ ጽፈው ለቀቁ።
ከሞይስ በኃላ በሪያን ጊግስ ጊዚያዊ አሠልጣኝነት የቆየው ዩናይትድ ሆላንዳዊ ሊዊስ ቫንሃል ላይ ትኩረቱ አርፏል። ባርሴሎና እና ባየርሙኒክን የመሳሰሉ ክለቦችን አሠልጥነው ውጤት ማምጣታቸው የኦልድትራፎርዱ መንበር አይከብዳቸውም ተብለውም ነበር።
ነገር ግን ክለቡ በሚፈለገው ልክ በፕሪሜር ሊጉ ተፎካካሪ አልኾነም። በአውሮፓ መድረኮችም የድሮ ጥንካሬው አብሮት አልተገኘም።

በሁለት ዓመት ቆይታቸው ክለቡን የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ማድረጋቸው እና የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫ ማስገኘት ዋስትና ሳይኾናቸው ቀርቶ ለስንብት ተዳርገዋል።
አወዛጋቢው ጆዜ ሞሪንሆ ቀጣዩ የዩናይትድ ቤት የፈተናቸው አሠልጣኝ፣ በዩናይትድ እና አርሴናል የፕሪሜር ሊጉ የበላይነት ላይ ውኃ የቸለሱ ናቸው ቸልሲን ይዘው። እናም ዩናይትድን ወደ ክብሩ ለመመለስ ተገቢው ሰው ስለመኾናቸው ብዙ እምነት ማግኘት ችለው ነበር።
ሞሪንሆ እንደተባለው በዩናትድ ቤት የተሻለ ተፎካካሪነት ፈጥረዋል። በቆይታቸው የዮሮፖ ሊግ እና ኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫ ማንሳታቸው ለዚህ ማሳያ ነው። በፕሪሜር ሊጉም የተሻለ ደረጃን አግኝተዋል።
ነገር ግን በአመላቸው የሚታሙት ሞሪንሆ ከተጫዋቾች ጋር የፈጠሩት እሰጣ ገባ ቆይታቸውን አሳጥሮታል።
ሞሪንሆን በጊዜያዊነት የተኩት ኦሌጉኖ ሶልሻየር ናቸው።

ሶልሻየር አጀማመራቸው ብዙዎችን አስደምሟል፤ ከመጀመሪያ 19 ጨዋታዎች 14ቱን በማሸነፍ ቋሚ ቅጥር ማግኘትም ችለው ነበር።
የሦስት ዓመታት ቆይታ የነበረው ሶልሻየር በቡድኑ ውስጥ የፈጠረው መልካም ሂደት በጊዜ ብዛት እየቀዘቀዘ ሄዷል። በቆይታው ይሄነው የሚባል ዋንጫ ሳያገኝም ስንብቱ ቀድሞታል።
ከሶልሻየር በኃላ ዩናይትድን ጀርመናዊ ራልፍ ራኚክ ለወራት በጊዚያዊነት አሰልጥነዋል። የእሳቸውን እግር ተከትለው ኦልድትራፎርድ የደረሱት ደግሞ ሆላንዳዊ ቴንሃግ ናቸው።
በአያክስ ከርቀት የሚታይ ሥራ ሠርተዋል። የሀገሪቱን ሊግ በተደጋጋሚ አንስተው ሲወደሱ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግም በማራኪ ጨዋታ ታላላቅ የተባሉ ክለቦችን በማሸነፍ የዩናይትድን ሰዎች ቀልብ ስበዋል።
ከፈርጉሰን በኃላ አምስተኛ ቋሚ አሠልጣኝ ኾነው ኦልድ ትራፎርድ የደረሱት ቴንሃግ የመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎችን በሽንፈት ነው ያጠናቀቁት።
ይሄን ተከትሎ የሰውየውን ብቃት የጠየቁ ብዙ ነበሩ። ነገር ግን በሂደት ቡድናቸውን አስተካክለው በዓመቱ መጨረሻ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ቦታን ማስገኘታቸው በጊዜ ሊበላቸው የነበረውን እሳት አጥፍቶላቸዋል።
የካራቦ ዋንጫን ሲያሸንፋም በጊዜ ሂደት ክለቡን ተፎካካሪ አንደሚያደርጉት ማሳያ ተብሎላቸዋል።

በ2023/2024 የውድድር ዘመን የዩናይትድ ደጋፊዎች የተሻለ ተፎካካሪ ቡድን እንደሚኖራቸው ጠብቀው ነበር። አሁን ላይ እውነታው ሲታይ ግን የአምናው የዩናይትድ መነቃቃት ከዚህ በፊት እንደታየው ታይቶ የሚጠፋ አይነት እንዳይኾን አስግቷል።
11 ሳምንታትን በዘለቀው የእንግሊዝ ፕሪሜር ሊግ የቴንሃጉ ቡድን በ18 ነጥብ ስምንተኛ ላይ ተቀምጧል።
አራት ጊዜ በነገሠበት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግም በአራት ጨዋታ ሦስት ነጥብ ብቻ አግኝቶ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ተገኝቷል።
አሰልጣኙ በመጀመሪያ ዓመታቸው ዋንጫ ባነሱበት ካራቦ ውድድርም በጊዜ ተሸኝተዋል።
አሰልጣኙ ከሮናልዶ ጋር የነበራቸው ውዝግብ በተሻለው ውጤታቸው ተሸፍኖ ቢያልፍም አሁን ተጫዋቾቻቸውን የሚይዙበት መንገድ እያስተቻቸው ነው።
ለውጤት መጥፋቱ መባባስም ራሳቸው ቤንዚን ኾነዋል ተብለው እየተተቹ ነው።

ይሄ ሁሉ ተጨማምሮ ቴንሃግ የኦልድ ትራፎርድ የመውጫ በር ላይ ስለመቆማቸው እየተነገረ ነው።
በቀጣይ ጨዋታዎች የሚያስመዘግቡት ውጤትም ቀጥታ የአሰልጣኙን ቆይታ ይወስናሉ ብሏል ቢቢሲ።
የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች ከምንም በላይ “በጥባጭ ጎረቤት” የሚሏቸው ሲቲዎች በፕሪሜር ሊጉ እያሳዩ ያሉትን የበላይነት የሚቋጭላቸው ኹነኛ አሰልጣኝ ይፈልጋሉ።
ማንቸስተር ሰማያዊ ናት የሚለው የጉረቤቶቻቸው ሽሙጥ እንቅልፍ አንደነሳቸው በማንሳት የክለባቸውን ተፎካካሪ መኾን ያለቀጠሮ ይፈልጉታል።
ጥያቄው ግን አስፈሪውን የኦልድ ትራፎርድ ግርማ ሞገስ ማን ይመልሰው የሚለው ነው። ለጊዜው ግን ተግባሩን የሞከሩ ሁሉ ፈተናውን አላለፉም።
ፈርጊ ለ27 ዓመታት ተደላድለው በ38 ዋንጫዎች የደመቁበት ወንበር የተቀመጡበትን ሁሉ እያቃጠለ እረፍት መንሳቱን ቀጥሏል።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የምንወዳትን ሀገራችንን ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ ኢትዮጵያዊ አብሮነትን ማስቀደም ይገባል” አቶ ይርጋ ሲሳይ
Next article“ልጆቻችን የኢትዮጵያን ችግሮች በሰው ሰራሽ አስተውሎት በመታገዝ ለመፍታት ቁልፍ የሆነውን እውቀት መገብየታቸው ተስፋ ሰጭ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)